የፌዴራል መንግሥቱ ለአዕምሮ ጤና ግልጋሎት መስጪያ የሚሆን የ$55 ሚሊየን የሽርክና ስምምነት ከታዝማኒያ መንግሥት ጋር ተፈራርሟል።
በስምምነቱ መሠረት $46 ሚሊየን ዶላርስ ወጪ በፌዴራል መንግሥቱ የሚሸፍን ይሆናል።
ገንዘቡ ሶስት የአዕምሮ ጤና ክሊኒኮችን በርኒ፣ ደቮንፖርትና ሆባርት መውጫ ላይ ለማቋቋሚያነት ይውላል።
ምርጫ ዝቅተኛ ደመወዝ
የፌዴራል በጅሮንድ ጆሽ ፍራይደንበርግ የተቃዋሚ ቡድን ፓርቲ የምጣኔ ሃብት ፖሊሲያቸው ግብታዊነት ላይ እንጂ በዕቅድ የተያዘ ፖሊሲ አይደለም በማለት ተችተዋል።
አቶ አልባኒዚ የዝቅተኛ ደመወዝ ማስተካከያ ከወቅቱ የዋጋ ግሽበት ጋር መመጣጠን እንዲችል የ 5.1 ፐርሰንት ጭማሪ እንዲደረግ የሚሹና ለፍትሐዊ የሥራ ኮሚሽንም ይህንኑ አስመልክተው በፅሁፍ እንደሚያቀርቡ ተናገረዋል።
ሆኖም አቶ ፍራይደንበርግ የመንግሥታቸው አቋም ጉዳዩን ለኮሚሽኑ መተው እንደሆነ ገልጠዋል።
በሌላ በኩል የአውስትራሊያ አገር አቀፍ የሠራተኞች ማኅበር የዝቅተኛ ደመወዝ ጭማሪ 5.5 ፐርሰንት እንዲሆን የሚሻ ሲሆን፤ የንግዱ ማኅበረሰብ ቡድን ጭማሪው ከሶስት ፐርሰንት እንዳያልፍ ይፈልጋል።
ቻይና - አውስትራሊያ - ሰለሞን ደሴቶች
በአውስትራሊያ የቻይና አምባሳደር ሺያዎ ቺያን ዛሬ ሐሙስ በአውስትራሊያን ፋይናንሻል ሪቪው ጋዜጣ ላይ ለህትመት ባበቁት መጣጥፋቸው አገራቸው ከፓስፊክ ደሴት አገራት ጋር የምታደርገው ትብብር ለአውስትራሊያ ስጋት አለመሆኑን አስፍረዋል።
ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ዋናው ጉዳይ ቻይና የምትለው ሳይሆን የምታደርገው ነው በማለት አሌ ብለውታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሚቀጥለው ሳምንት ሰለሞን ደሴቶችን እንደሚጎበኙ ተነግሯል።