የተቃዋሚ ቡድን መሪ አንቶኒ አልባኒዚ በሜዲኬይር የሚደጎሙ የሙከራ 50 የአስቸኳይ የጤና ክሊኒኮች በመላ አውስትራሊያ ግብር ላይ እንደሚያውሉ አስታወቁ።
ክሊኒኮቹ ግብር ላይ እንዲውሉ የሚደረጉት በሆስፒታል ያሉ የድንገተኛ አስቸኳይ ዲፓርትመንቶችን መጨናነቅ በመቀነስ ለቤተሰቦች የተሻለ አማራጭ የሕክምና ግልጋሎቶችን መስጠት ያስችላሉ ከሚል ዕሳቤ ነው።
የሚያተኩሩባቸው የሕክምና ግልጋሎት ዘርፎችም የአጥንት ስብራት፣ አንስተኛ የአካል ቃጠሎና የተቆረጠ የሰውነት ክፍልን መስፋት ናቸው።
ለአስቸኳይ የጤና ክሊኒኮቹ መደጎሚያ በአራት ዓመታት ውስጥ $135 ሚሊየን ዶላርስ በጀት የሚመደብላቸው ይሆናል።
አቶ አልባኒዚ የክሊኒኮቹ ግልጋሎቶች ሜዲኬርን የማጠናከሪያ እርምጃም እንደሆነ አስታውቀዋል።
ነዳጅ
ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ለድፍድፍ ነዳጅ ማጣሪያ የሚውል $250 ሚሊየን መመደባቸውን አስታወቁ።
ከበጀቱ ውስጥ $125 ሚሊየን ዶላር ለቪቫ ኢነርጂ እና አምፖል ድፍድፍ ነዳጅ ማጣሪያ ኩባንያዎች በጥሬ ገንዘብ ለድጎማ የሚውል ይሆናል።
አቶ ሞሪሰን ጂሎንግ ከኢነርጂ ሚኒስትር አንገስ ቴይለር ጋር ሆነው ሲናገሩ፤ ድጎማው ለአውስትራሊያ የወደፊት የነዳጅ አቅርቦት ዋስትና እንደሚበጅና ተጨማሪ የሥራ ዕድልም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

Prime Minister Scott Morrison meets refinery workers during a visit to Geelong Oil Refinery on Day 3 of the 2022 federal election campaign. Source: AAP
ተጨማሪው $125 ሚሊየን ዶላር ለኩዊንስላንድ የተመደበ መሆኑን ገልጠዋል።
የጥርስ ሕክምና
የግሪንስ ፓርቲ መሪ አደም ባንድት በዘንድሮው ምርጫ ፓርላማ ውስጥ የኃይል ሚዛን ለማግኘት ከበቃ ከ$77 ቢሊየን በላይ በአንድ አሠርት ዓመት የሚያወጣ የጥርስ ክብካቤ ዕቅድ እንዳላቸው ይፋ አድርገዋል።
ዕቅዱ አውስትራሊያውያን በሜዲኬይር የሚሸፈን የጥርስ ክብካቤ ሕክምና እንዲያገኙ የሚያደርግ መሆኑን በመግለፅ የፓርቲያቸውን ፖሊሲ ገልጠዋል።
አክለውም፤ ባለፈው ወቅት ግሪንስ የኃይል ሚዛን ይዞ በነበረበት ወቅት ለልጆች የጥርስ ሕክምና ከሜዲኬይር ጋር እንዲያያዝ ማስደረግ መቻሉን ጠቁመው ዘንድሮም ፓርቲያቸው ዕድሉ ከገጠመው በሜዲኬይር የሚሸፈን የጥርስ ክብካቤ ለሁሉም ለማስገኘት እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

Greens leader Adam Bandt addresses the National Press Club in Canberra on Wednesday. Source: AAP
ዋን ኔሽን ፓርቲ
የቀድሞው የኩዊንስላንድ ሊብራል ናሽናል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ጆርጅ ክሪስቴንሰን በዘንድሮው የሜይ 21 አገር አቀፍ ምርጫ ዋን ኔሽን ፓርቲን ወክለው እንደሚወዳደሩ አስታወቁ።
አቶ ክሪስቴንሰን በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ከሊብራል ናሽናል ፓርቲ አባልነታቸው የለቀቁ ሲሆን፤ ከዳውሰን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነታቸው በዚህ ወር መጨረሻ የሚለቁ ይሆናል።
አቶ ክሪስቴንሰን በዘንድሮው ምርጫ ዋን ኔሽንን ወክለው የሚወዳደሩት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሁን ወይም ለሕግ መወሰኛ ምክር ቤት መሆኑ አልተገለጠም።

One Nation leader Pauline Hanson and her new Senate candidate George Christensen. Source: AAP