ከዛሬ ሰኞ ፌብሪዋሪ 13 / የካቲት 6 አንስቶ የአውስትራሊያ መንግሥት በጊዜያዊ ቪዛዎች ያሉ ነዋሪዎች ለቋሚ ቪዛ ማመልከት እንደሚችሉ አስታወቀ።
የኢሚግሬሽን ሚኒስትር አንድሩ ጂለስ በተለይ በጊዜያዊ ቪዛ ያሉ ነዋሪዎች ለ10 ዓመታት እርግጠኝነት አልባ በሆነ ሁኔታ ውሳኔን ሲጠብቁ እንደቆዩ አመላክተዋል።
ለቋሚ ቪዛ ማመልከት የሚችሉት የሉዓላዊ ድንበሮች ዘመቻ ድንጋጌ ግብር ላይ ከመዋሉ በፊት ወደ አውስትራሊያ የዘለቁ ባለ ጊዜያዊ ቪዛ ባለቤቶችን ነው።
ማመልከቻቸውን አስገብተው ቋሚ ቪዛ የሚያገኙ ሰዎች ቋሚ ቪዛ ያላቸው ነዋሪዎች የሚያገኟቸውን መብቶችና ጥቅሞች ሁሉ የሚያገኙ ይሆናል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ ጉዳያቸው ታይቶ ጥበቃ ለማግኘት ብቁ ያልሆኑና የአቤቱታ ክለሳ የማይጠብቁ ግለሰቦች አውስትራሊያን ለቅቀው እንዲወጡ የሚደረግ መሆኑን የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ክሌየር ኦኒል አስታውቀዋል።
ብሔራዊ ይቅርታ
የተሰረቁ ትውልዶችን አስመልክቶ የተካሔደው ብሔራዊ የይቅርታ ቀን ዛሬ ሰኞ ፌብሪዋሪ 13 / የካቲት 6 በመዲናይቱ ካንብራ በቁርስ ሥነ ሥርዓት ታስቧል።
በ2008 የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኬቨን ራድ የአውስትራሊያ ነባር ዜጎች ባለፉት መንግሥታት ሕፃናትን ከወላጆች የመነጠል ፖሊሲዎች ሳቢያ ለመንፈስ ጭንቀትና ጥበት መዳረግን አስመልክቶ ብሔራዊ ይቅርታን ጠይቀዋል።
ይህንኑ አስመልክቶ ሴናተር ፓት ዶድሰን ለABC በሰጡት መግለጫ ብሔራዊ ይቅርታው የቁርሾ ፈውስ ጅማሮ መሆኑን ገልጠዋል።