የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሪት ፍሬህይወት ታምሩ የተቋሙን የስራ አፈጻጸም በተመከከተ ባቀረቡት ማብራሪያ እንደተናገሩት ባለፈው ስድስት ወራት ድርጅቱ ለውድድሩ ገበያ ብቁ እንዲሆን የኔትወርክ ማስፋፊያ ብሎም የማኅበረሰቡን አቅም ታሳቢ ያደረገ ታሪፍ የያዘ ስትራቴጂ ቀርጾ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል።
የሶስት ዓመት ስትራቴጂ በዋናነት መሪ ዲጂታል መፍትሄዎች አቅራቢ፣ ከፍተኛ የደንበኛ ልምድ፣ ቀጣይነት ያለው የንግድ ዕድገት፣ በቴክኖሎጂ እና መፍትሄዎች የላቀ፣ የተግባር ልቀት ያለው ባለሙያዎችን ያማከለ በመሆን ከፍተኛ አፈጻጸም ያለው ኩባንያ እንዲሆን ማድረግ መቻሉንም ፍሬህይወት ተናግረዋል።
ኢትዮቴሌኮም ለSBS ባደረሰው መረጃ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እሴትን ይጨምራሉ የተባሉ ሥራዎችን ባለፉት ስድስት ወራት የተሰራ ሲሆን፤ በዚህም የደንበኞች ብዛት ወደ 70 ሚሊዮን እንዲደርስ ማድረግ ተችሏል ብሏል።
67.7 ሚሊዮን ደንበኞች የድምጽ ጥቅል ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለፀው ኩባንያው ባለፉት ስድስት ወራት ኩባንያው 9.2 ሚሊዮን ተጨማሪ ደንበኞች ማፍራት በመቻሉ ይህ አፈፃፀሙ የእቅዱን 99.9 በመቶ ማሳካት እንዳስቻለው ገልጿል።
ኢትዮ-ቴሌኮም በ2014 በጀት ዓመት ዘጠኝ ቢሊየን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ገልፆ በያዝነው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ብቻ 8.18 ቢሊየን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ገልጧል።
ለትርፍ እድገቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገውም ኩባንያው የተገበረው የወጪ ቅነሳ ስራ እንደሆነ አክሎ አስታውቋል።
ኢትዮ-ቴሌኮም በወጪ ቅነሳ 3.5 ቢሊየን ብር ለማዳን የቻለ ሲሆን፤ በመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት 33.8 ቢሊየን ብር ገቢ አግኝቷል። በዚህም የእቅዱን 96 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልፀዋል።
ገቢው ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ20 በመቶ የ5.62 ቢሊየን ብር ዕድገት ማሳየቱን የገለፀው ኩባንያው 91 አዳዲስ እና የተሻሻሉ አገልግሎቶች አቅርቧል።
በውጪ ምንዛሪ 64.8 ሚሊየን ዶላር ገቢ ማስገባቱ ተገልጿል።
[ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ ]