የዝነኛው "የሮክ ንጉሥ" ኤልቪስ ፕሪስሊ ብቸኛዋ ሴት ልጅ ሊዛ ሜሪ ፕሪስሊ በልብ ሕመም ሳቢያ በ54 ዓመቷ ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች።
የሊዛ ሜሪ ዜና ዕረፍት የተገለጠው በእናቷ ፕሪስኪላ ፕሪስሊ ነው።
ፕሪስኪላ የልጇን ሕልፈተ ሕይወት ስትገልፅ "የውቧን ሴት ልጄን ሊዛ ሜሪ ከእኛ የመለየት ዜና ዕረፍት ከጥልቅ ልባዊ ሐዘን ጋር ላጋራችሁ ግድ ይለኛል" ስትል ለፒፕል መፅሔት ገልጣለች።
ሊዛ ሜሪ ወደ ሆስፒታል የተወሰደች ቢሆን የልቧ ምት አቁሞ ከዚህ ዓለም ተለይታለች።
ባለፈው ማክሰኞ ዕለት ሎስ አንጀለስ ውስጥ በተካሔደው 80ኛው ወርቃማ ሉል ሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝታ የአባቷን የሕይወት ታሪክ "ኤልቪስ" ፊልም በዋነኛ ገፀ ባሕሪይነት የተወነውና "ምርጥ ተዋናይ" ተብሎ የተሸለመው ኦስቲን በትለር ሽልማት ሲወስድ በታዳሚነት ተገኝታ ነበር።