ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ዛሬ ዓርብ በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በመንግሥታዊ አመራራቸው ወቅት "በመጠኑ የቡልዶዘር" አመራርን መተግበር ግድ ይል እንደነበር አመላክተው፤ ሆኖም ዳግም ከተመረጡ የአመራር ስልት ለውጥ እንደሚያደርጉ ገለጡ።
አቶ ሞሪሰን የአመራር ለውጥ ሊያደርጉ እንደሚችሉ የገለጡት አውስትራሊያውያንን ይበልጥ ቀርበው መስማት ያለባቸው እንደሁ በተጠየቁበት ወቅት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው "አውስትራሊያውያንን መስማት በጣም ጠቃሚ ነው፤ በፖለቲካ ሙያዬ ወቅት ሁሉ ያንን አድርጌያለሁ"
"ወደ ሁኔታዎች ሲመጣ በመጠኑ ቡልዶዘር መሆን እንደምችል እኔም አውቃለሁ፤ አውስትራሊያውያንም ያውቃሉ" ብለዋል።
ይህንኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አባባል ተከትሎ የሌበር መሪ ፈጥነው በሰነዘሩት ምላሽ፤
"ዛሬ ስኮት ሞሪሰን ቡልዶዘር መሆናቸውን ተናግረዋል። ቡልዶዘር ነገሮችን ያፈርሳል፣ ቡልዶዘር ነገሮችን ይገረስሳል። እኔ ገንቢ ነኝ። ያ ነኝ እኔ"
"ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኜ ከተመረጥኩ እዚህ አገር ውስጥ ነገሮችን እገነባለሁ። ስኮት ሞሪሰን ለእኔ ድምፅ ስጡ፤ እናም እለወጣለሁ ብለዋል። ለውጥ የምትሹ ከሆነ፤ የመንግሥት ለውጥ አድርጉ" ብለዋል።