ዛሬ ሐሙስ ኤፕሪል 13 አራት የጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን የደኅንነት ጥበቃ አባላት ለሆስፒታል ተዳርገዋል።
አደጋው የደረሰባቸው አራት የፖሊስ ሠራዊት አባላት ሲሆኑ፤ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ከአውስትራሊያ ፌዴራል ፖሊስ፤ ሁለት ወንዶች የታዝማኒያ ፖሊስ አባላት ናቸው።
አራቱ የፖሊስ ሠራዊት አባላት የደረሰባቸው አደጋ ለሕይወታቸው አስጊ እንዳልሆነ ተነግሯል።
በአደጋው ሳቢያ ዛሬ ከቀትር በኋላ ሊካሄድ ታስቦ የነበረው የጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን የምርጫ ዘመቻ ተቋርጧል።
አቶ ሞሪሰን በራሳቸውና በቤተሰባቸው ስም ለደኅንነት ጥበቃ አባላቱ ምስጋና አቅርበዋል፤ በፍጥነት እንዲያገግሙም መልካም ምኞታቸውን ገልጠዋል።
የሌበር ፓርቲ መሪ አንቶኒ አልባኒዚም አደጋው ለደረሰባቸው የደኅንነት አባላት በቶሎ እንዲያገግሙ መልካም ምኞታቸው ገልጠው፤ ስለ አገልግሎታቸውም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ለጥበቃ አባላቱ ቤተሰቦችም ስለ አደጋው ገለጣ ተደርጓል።
ከፖሊስ ሠራዊት አባላቱ መኪና ጋር የተጋጨው የሌላኛው መኪና ሾፌር ላይ የደረሰ ጉዳት የለም።
የአደጋው መንስዔ እየተመረመረ ይገኛል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ከአደጋው በፊት ረፋዱ ላይ በ2019 የምርጫ ዘመቻ ወቅት የ2022 ምርጫ ከመጠራቱ በፊት ባሉት ሶስት ዓመታት ውስጥ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ለማቋቋም የገቡት የምርጫ ቃል ማጠፋቸውን ተጠይቀው ሲመልሱ "በሌበር ፓርቲ ስላልተደገፈ እንጂ የምርጫ ቃሌን አጥፌ አይደለም" ብለዋል።
ሆኖም የዘርፉ ተጠባቢዎች የአቶ ሞሪሰን ረቂቅ የፀረ ሙስና ድንጋጌ በማንም ዘንድ ድጋፍ ያለው ስላልነበረ እንጂ ለፓርላማ ቀርቦ በሌበር በኩል ድጋፍ የተነሳው እንዳልሆነ አመላክተዋል።
በሌላም በኩል፤ የተቃዋሚ ቡድን መሪ አንቶኒ አልባኒዜ ባሕር ማዶ ያሉት የጥገኝነት እገታ ማዕከላት እንዳሉ እንደሚቆዩና በጀልባ ተጭነው የሚመጡ ጥገኝነት ጠያቂዎችም ወደ መጡበት እንዲመለሱ ግብር ላይ እየዋለ ያለው የመንግሥት ፖሊሲ ፀንቶ እንዲቀጥል የሚያደርጉ መሆኑን አስታውቀዋል።
የተቃዋሚ ቡድን መሪው ዛሬ የምርጫ ዘመቻቸውን ያካሔዱበትን በኒው ሳውዝ ዌይልስ የሚገኘው የሃንተር ቫሊ ምክር ቤት ወንበር ከሌበር እጅ ሳይወጣ እንደሚዘልቅ ያላቸውን ተስፋ ገልጠዋል።