የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት ትናንት ኤፕሪል 13 ባካሔደው ስብሰባ ወሲባዊ ጥቃትን እንደ ጦር መሣሪያነት መጠቀምን ለማክሰም እየሠሩ ያሉት የተመድ ዋና ፀሐፊ ልዩ ወኪል ፕራሚላ ፓቴን በሥፍራው ተገኝተው ለሰለባዎች ፍትሕን፣ እንዲሁም ወሲባዊ ጥቃትን በቅድሚያ ስለ መከላከል አበክረው ተናግረዋል።
አክለውም፤ ምክር ቤቱ ሴቶች፣ ሰላምና ፀጥታን አስመልክቶ 10 እንዲሁም ከግጭት ጋር የተያያዙ ወሲባዊ ጥቃቶችን ማመልከትንና ቅድመ መከላከል ማድረግን አስመልክቶ አምስት የአቋም መግለጫዎችን ማሳለፉን አንስተው፤ የእወጃዎቹ እርባና በአሁኑ ወቅት ለዩክሬይን፣ አፍጋኒስታንና ሚያንማር ወይም ለሰሜናዊት ኢትዮጵያ ትግራይ ሴቶች ምን ማለት እንደሆነ ጠይቀዋል።
ወሲባዊ ጥቃትን እንደ ጦር መሣሪያነት መጠቀምን ያመላክተው ዓመታዊው ሪፖርት የ2020 ጥቃቶችን ያዘለና 18 አገራትን ያካተተ ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት 3,293 በተመድ የተረጋገጡ ጥቃቶችንም ይዟል።
ጥቃቶቹ 97 ፐርሰንት ያህሉ ሴቶችና ልጃገረዶችን ዒላማ ያደረጉ ስለመሆኑ፣ 83 እገታ ማዕከላት ውስጥ ወሲባዊ ጥቃቶች የተፈፀመባቸውን አዋቂና ወጣት ወንዶችን፤ እንዲሁም 12 የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ላይ የተፈፀሙ መሆናቸውንም ሪፖርቱ አመልክቷል።
ሪፖርቱ የድርጊት ዒላማ ላይ ያነጣጠረ ቅድመ መከላከል ለማድረግ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ተሳትፎዎች እንዲካሔዱ፣ ወሲባዊ ጥቃትን በተኩስ አቁምና የሰላም ስምምነቶች ወቅት እንዲነሳ፣ ቅድመ የወሲባዊ ጥቃት ማስጠንቀቂያና ትንተና እንዲደረግ፣ አነስተኛ የጦር መሳሪያ ፍሰትን መገደብ፣ ጾታ ተኮር ፍትሐዊ የአፀፋ እርምጃ እንዲወሰድ፣ የፀጥታ መስክ ማሻሻያ ለውጥና የሰለባዎች ድምፆች ጎልተው እንዲሰሙ ማድረግ የሚሉ ምክረ ሃሳቦችን አያይዞ አቅርቧል።
ወ/ሮ ፓቴንም በበኩላቸው ዶክሜንቶቹ ከታይታነት አልፈው ለሕጋዊ ተጠያቂነት የሚበያቁ እንዲሆኑ አሳስበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ ከኢራቅ፣ ሶሪያና ኢትዮጵያ ሴቶች በኩል ወሲባዊ ጥቃቶችን አስመልክተው እማኝነታቸውን አስደምጠዋል።
በኢትዮጵያ በኩል ኅሊና ብርሃኑ የትግራይ ጉብኝታቸውን አንስተው ወሲባዊ ጥቃት እንደ ጦር ስልት አለያም ለበቀል መወጫነት እንደዋለ ተናግረዋል።
አክለውም፤ ጥቃቱ ዘር ላይ ያተኮረ እንደሆነና ሰለባዎቹንና ማኅበረሰባቱን ለማዋረድም እንደዋለ አመላክተው፤ ለትግራይና ሌሎች ሥፍራዎችም የአዕምሮ ጤና እገዝ እንዲደረግ ለምክር ቤቱ ታዳሚ አምባሳደሮች አሳስበዋል።