በኢፌዴሪ ወታደራዊ አመራሮችና በኦሮሞ ነፃነት ታጣቂዎች ታንዛኒያ መዲና ዳሬሰላም የተጀመረው የሰላም ንግግር ወደ ሁለኛ ምዕራፍ ተሸጋግሮ በፖለቲካ አመራር ተወካዮች መካሔድ መጀመሩን ቅርብርት ያላቸው ምንጮች ገልጠዋል።
በመንግሥት በኩል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የጠቅላይ ሚንስትሩ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪና የፍትሕ ሚኒስት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ የሰላም ውይይቱን በተወካይነት ለማካሔድ ሕዳር 2 ዳሬሰላም መግባታቸው ተነግሯል።
በታካይነትም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ባለስልጣናት ከታጣቂዎቹ አመራር አባላት ጋር መነጋገራቸው ተጠቁሟል።
የመጀመሪያው ውይይት የተጀመረው ጥቅምት 27 ቀን 2016 ሲሆን፤ ለውይይቱ ስኬት የአሜሪካ፣ የኢጋድ፣ ኬንያና ኖርዌይ መንግሥታት ተወካዮች ድጋፍ እየቸሩ መሆኑም ተመልክቷል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሶስተኝ ዓመት አራተኛ መደበኛ ስብሰባ በዛሬው ዕለት ተከናውኗል።
በሂደቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሕዝብ ተወካዮች ለቀረቡላቸው ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች ምላሾችን ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጧቸው ምላሾች ሰላምና ደሕንነት፣ የመከላከያ ሠራዊትና የኢትዮጵያ ሕልውና፣ የብዙኅን መገናኛ ዘገባዎችን፣ የልማት ሥራዎችን፣ የትምህርት፣ ምጣኔ ሃብት፣ ሙስናንና በክልሎች መካክል ያሉ የይገባኛል ወሰን ልዩነቶችን አንስተዋል።
በተለይም በትግራይና በአማራ ክልል ያለውን "አከራካሪ በሆኑ" አካባቢዎች ብለው ለጠሩት የይገባኛል ጥያቄ መፍቻ መንግሥታቸው ይዞት ያለው አማራጭ መፍትሔ ሕዝበ ውሳኔ እንደሆነ አመላክተው "ሌላ የመፍትሔ ሃሳብ ካለ የፌዴራል መንግሥት በደስታ" እንደሚቀበል ተናግረዋል።
አክለውም፤ የአማራና ኦሮሞ ሕዝቦች "ፈለጉም አልፈለጉም በሰላም ለመኖር ያላቸው ምርጫ አንድ ብቻ ነው፤ይህም የአንድ አባት ልጆች ፣ የአንድ ሀገር ዜጎች ወንድማማቾች መሆናቸውን አውቀው በሰላም በተከባበረ አብሮ መኖር በሚያስችል ማንነት መጉዋዝ ብቻ ነው" ብለዋል።