የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነሐሴ 8 ከቀትር በኋላ በአካሔደው አስቸኳይ ስብሰባ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ በተመራለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አጀንዳ ላይ ተነጋግሮ በ332 የድጋፍ ድምፅ ይሁንታውን ቸሯል።
በድምፅ አሰጣጡ ሥነ ሥርዓት ወቅትም 16 ተቃውሞና 12 ድምፀ ተዐቅቦ ተመዝግቧል።
በዕለቱ በአስቸኳይ ስብሰባው ላይ 330 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ታድመዋል።
በስብሰባው ላይ የቀድሞው የአማራ ክልል ፕሬዚደንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ባሰሙት ንግግር እሳቸው የሚወክሉት ጥቂት ፅንፈኞችን ሳይሆን የአማራን ሕዝብ መሆኑን አስገንዝበው "የአማራ ሕዝብ ችግር ፖለቲካዊ ችግር ነው። ለፖለቲካዊ ችግር ፖለቲካዊ መፍትሔ እንጂ ወታደራዊ መፍትሔ አያሻውም" ብለዋል።
አክለውም "የመከላከያ ሠራዊቱ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ካምፑ ይመለስ፤ ሁሉንም የአማራ ኃይሎች ያቀፈ ጊዜያዊ አስተዳደር ይቋቋም" ሲሉ ጠይቀዋል።