ከተቃዋሚ ቡድን በኩል ድጋፍ የተነፈገውና በግል ተመራጮች ዘንድ እምብዛም ገፍቶ አልሔደም የሚል ትችት የቀረበበት የፌዴራል መንግሥቱ የጋዝ ዋጋ ንረት እፎይታ ረቂቅ ሕግ በአብላጫ ድምፅ በምክር ቤት ይሁንታን አግኝቶ ፅድቅ ተቸሮታል።
በፓርላማ ክርክር ወቅት የተቃዋሚ ቡድኑ ረቂቅ ሕጉ የገበያ ጣልቃ ገብነት ያደርጋል፤ የዋጋ ቅናሽም አያስገኝም ብሎ ስለሚያምን ድጋፉን እንደማይቸር መሪው ፒተር ዳተን አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኢስትር አንቶኒ አልባኒዚ በበኩላቸው ተቃዋሚ ቡድኑ "ለመራጮች ደህንነት ተጨናቂ አይደለም" ሲሉ የአፀፋ ምላሻችውን ሰጥተዋል።
ምንም እንኳ በጋዝ ዋጋ ላይ የጣራ ገደብ የተጣለው የኤሌክትሪክ ኃይል ዋጋ ጭማሪንም ለመቀነስ ቢሆንም፤ በመጪው 2023 የፋይናንስ ዓመት በሩስያና ዩክሬይን ጦርነት ሳቢያ አሁን አውስትራሊያውያን ላይ ተጭኖ ባለው 20 ፐርሰንት የዋጋ ጭማሪ ላይ ታካይ 36 ፐርሰነት የዋጋ ንረት ሊከሰት እንደሚችል ከወዲሁ የዐቃቤ ንዋይ ጽሕፈት ቤት ጠቁሟል።
የፌዴራል መንግሥቱ በወሰደው ብርቱ እርምጃ የጋዝ ዋጋ በጊጋጁል 12 ዶላርስ ላይ እንዲረጋ ሲያደርግ፤ ያም በሚቀጥለው የፋይናንስ ዓመት የ23 ፐርሰንት የኤሌክትሪክ ዋጋ ንረትን ይገታል።
በርካታ የግል ተመራጭ የምክር ቤት አባላት ግና ከጦርነቱ በፊት የጋዝ ዋጋ $9.20 የነበረና ለኩባንያዎቹም በእጅጉ አትራፊ በመሆኑ የ12 ዶላር የዋጋ ገደብ በቂ አይደለም ሲሉ የመከራከያ ሃሳባቸውን አስደምጠዋል።
በፌዴራል መንግሥቱ "የዋጋ እፎይታ ዕቅድ" መሠረት ለኑሮ አቅም ማነስ ተጋላጭ ለሆኑ አውስትራሊያውያን በፌዴራልና ክፍለ አገር መንግሥታት በጋራ የሚከፈል 3 ቢሊየን ዶላርስ መመደቡን የፌዴራል በጅሮንድ ጂም ቻልመርስ ገልጠዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያለፈው ድንጋጌ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱን ድጋፍ አልፎ ለሕኘት የበቃው በግሪንስ ፓርቲና የግል ተመራጭ ምክር ቤት አባላት ድጋፍ ነው።
በሌላም በኩል ባለፈው ሳምንት የመከረውን የብሔራዊ ምክር ቤት ስምምነት ተከትሎ የደንጊያ ከሰል ዋጋ በክፍለ አገር መንግሥታት አማካይነት በቶን የ125 ዶላር ጣራ ገደብ ይጣልበታል።