የጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዝን የሁለት ቀናት ጉብኝት ተከትሎ የአውስትራሊያንና ፓፕዋ ኒው ጊኒንን የሁለትዮሽ ግንኙነት በይበልጥ ለማጠናከር ተጨማሪ ዕቅድ ተይዟል።
አውስትራሊያ ለፓፕዋ ኒው ጊኒ የውጭ ዕርዳታዋን ያጠናከረች ሲሆን፤ ያም "ለአውስትራሊያ ብሔራዊ ጥቅም" ከፍ ያለ ፋይዳ እንደሚኖረው አቶ አልባኒዚ አመላክተዋል።
የአውስትራሊያ ተገማች 2022-23 የውጭ ዕርዳታ በጀት $500 ሚሊየን ሲሆን፣ ለፓፕዋ ኒው ጊኒ የሚውለው ዕርዳታ ለሴቶች አመራር ብቃት ማዳበሪያ፣ ለትምህርት ማስፋፊያና የጤና ሥርዓት ማጠናከሪያ እንደሚውል ተገልጧል።
እሥራኤል
በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ እሥራኤውያን የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁን የሕግ ማሻሻያ ትልም ተቃውመው የአደባባይ ሰልፍ አካሂደዋል።
ኔታንያሁና ወግ አጥባቂ ሃይማኖታዊ ብሔረተኛ ቅንጅት አጋሮቻቸው የመንግሥትን ሶስትዮሽ ቅርንጫፍ 'ሚዛን ለማስጠበቅ' በሚል አስባብ
የጠቅላይ ፍርድ ቤትን ውሳኔ ለመቀልበስ የሚያስችል ረቂቅ ድንጋጌ ነድፈዋል።
ረቂቅ ድንጋጌው የፍትሕ ሥርዓቱን ነፃነት ያሽመደምዳል፣ ሙሰኝነትን ያስፋፋል፣ የአናሳ ወገኖችን መብቶች ይሸርፋል የሚሉ ብርቱ ትችቶችን ከወዲሁ አስከትሏል።
የተቃውሞ ሰልፉን ላይ ከተገኙት የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች አንዱ የሆኑት ጂል ሊብርውስኪ ስለ ምን ለተቃውሞ ሰልፍ አደባባይ እንደወጡ ሲናገሩ " ለተቃውሞ ሰልፍ የወጣሁት ዲሞክራሲያችንና የፍትሕ ተቋማችንን ከመነጠቅ ለመከላከል ነው። ጠንካራና ነፃ የፍትሕ ሥርዓት ያሻናል፤ መንግሥታችን ግና ሊከላው ይፈልጋል። ፕሬዚደንቱን በማናገር ያ ዕውን እንዳይሆን እንዲያደርጉና ከእኛ ወገን እንዲቆሙ ለማድረግ እየጣርን ነው" ብለዋል።