የተርክዬ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ አሸናፊ ውጤት በይፋ በምርጫ ኮሚሽን በኩል ባይነገረም ከሁለቱም ዕጩ ፕሬዚደንቶች በኩል አሸናፊነታቸውን እየገለጡ ነው።
እስካሁን 80 ፐርሰንት ያህል የመራጮች ድምፅ ተቆጥሯል።
ፕሬዚደንት ኢርዶጋንና ተቀናቃኛቸው ከማል ኪሊችዳሮሉ በየፊናቸው አሸናፊነታቸውን ቢገልጡም ሁለቱም ከ45 ፐርሰንት የዘለለ ድምፅ አላገኙም።
ከሁለቱ ዕጩ ፕሬዚደንቶች አንዳቸው 50 ፐርሰንት ላይ ካልደረሱ ሜይ 28 ዳግም ምርጫ ይካሔዳል።
የፕሬዚደንት ኢርዶጋን ፓርቲ ቃል አቀባይ አቶ ኢርዶጋን በምርጫው ውጤት እየመሩ ቢሆንም፤ የምርጫ ኮሚሽኑን ይፋዊ ወጤት እንደሚያከብሩ ተናግረዋል።
የናዚ ሰላምታ
በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በቪክቶሪያ ፓርላማ ፊት ለፊት የተካሔደውን ፀረ ኢሚግሬሽን ሰልፍ ተከትሎ የቪክቶሪያ መንግሥት የናዚ ሰላምታን በአፋጣኝ እንዲያግድ ጥያቄዎች ቀርበዋል።
የቪክቶሪያ ፖሊስ ቅዳሜ ዕለት በናዚ ሰላምታ ሰጪዎችና ተፃራሪዎች መካከል በተካሔደው ግጭት አለመደስቱን ገልጧል።
ፖሊስ ግጭቱን በቁጥጥር ስር ለማዋል እንደቻለና ጥቁር ለብሰው ከነበሩት 20 ያህል የተቃውሞ ሰልፈኞች ውስጥ ሁለቱን ለእሥር መዳረጉን አስታውቋል።
በዲከን ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር ጆሽ ሮዝ፤ የናዚ ሰላምታን ለማገድ ሂደቱ ረጅምና አዋኪ እንደሚሆን አመላክተዋል።