ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ዛሬ እኩለ ቀን ላይ የሊብራል ፓርቲን ይፋ የአገራዊ ምርጫ ዘመቻ ብሪስበን ከተማ ከፍተዋል።
አውስትራሊያ ከወረርሽኙ አልፋ አንገቷን ቀና አድርጋ ለመቆም መብቃቷንም ጠቅሰዋል።
የምርጫ ዘመቻ መክፈቻ ስብሰባው በተካሔደብት የብሪስበን ጉባኤ ማዕከል የቀድሞ የሊብራል ጠቅላይ ሚኒስትራት ጆን ሃዋርድና ቶኒ አበት ተገኝተዋል።
ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን የተኳቸው የሊብራል ጠቅላይ ሚኒስትር ማልከም ተርንቡል በሥፍራው አልተገኙም።

Former prime minister Tony Abbott (L), Jeanette Howard (C), and husband former prime minister John Howard (R). Source: AAP
ከቶውንም አቶ ተርንቡል ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ዛሬ ይፋ ያደረጉትን ከጡረታ አበል ተቀማጭ ላይ ወስዶ ቤት የመግዛት ፖሊሲ "እብደት የተመላው ዕሳቤ" ሲሉ አክርረው ተችተዋል።
በአዲሱ ፖሊሲ መሠረት 1.3 ሚሊየን ያህል ዕድሜያቸው ከ55 በላይ የሆኑ ሰፋፊ ቤቶቻቸውን ሸጠው ወደ አነስተኛ ቤት በመቀየር እስከ $300,000 በግለሰብ ደረጃ ወደ ጡረታ አበላቸው መጨመር ይችላሉ።

Malcolm Turnbull, former Australian Prime Ministel. Source: Getty
ይህም ወጣት ቤተሰቦች ሰፋፊ ቤቶችን ለመግዛት የሚያስችል መሆኑ ተነግሯል።
አቶ ሞሪሰን መንግሥታቸው ዳግም ከተመረጠ የመጀመሪያ ቤት ገዢዎች ከጡረታ አበል ተቀማጫቸው እስከ 50 ሺህ ዶላርስ ወጪ በማድረግ ለቤት ግዢ የቅድሚያ ተቀማጭ ክፍያ ማድረግ እንዲችሉ የሚፈቅድ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የቀድሞው የሌበር ጠቅላይ ሚኒስትር ፓል ኪቲንግ ግና "ሊብራሎች ከመነሻው የጡረታ አበል ተቀማጭ ሥርዓትን ይጠላሉ። ሠራተኛ አውስትራሊያውያን በጡረታ ዘመናቸው ከመንግሥት ነፃ ሆነው ሃብት እንዳይኖራቸው ይቃወማሉ" በማለት የሊብራል ፓርቲ ፖሊሲ ላይ ነቀፌታ ሰንዝረዋል።
አቶ ሞሪሰን በመጀመሪያው ዙር የሶስት ዓመት ተኩል ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ገና "እየተሟሟቁ" እንደሁ ጠቅሰው አውስትራሊያውያን ዳግም እንዲመርጧቸው ጠይቀዋል።

A general view as Australian Prime Minister Scott Morrison addresses the crowd at the Liberal Party election campaign launch on May 15, 2022 in Brisbane. Source: Getty
ተቀናቃኛቸው የሌበር ፓርቲ መሪ አቶ አንቶኒ አልባኒዚም ብሪስበን ከተማ ተገኝተው ለደጋፊዎቻቸው ንግግር አድርገዋል።