የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት መስከረም 3, 2015 / ሴፕቴምበር 13, 2022 ባወጣው የሐዘን መግለጫ በዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ ሕልፈተ ሕይወት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገለጠ።
በዘውድ ምክር ቤቱ ፕሬዚደንት ልዑል ኤርሚያስ ሣህለ ሥላሴ ኃይለ ሥላሴ አማካይነት ሐዘኑን የገለጠው ምክር ቤት፤ ንግሥት ኤልሳቤጥ ከኢትዮጵያ ጋር የነበራቸውን ጥልቅ ግንኙነትና ያበረከቷቸውንም አስተዋፅዖዎች ዋቤ ነቅሶ በማመላከት ነው።
አያይዞም፤ በንግሥቲቱ ሕልፈት ጥልቅ ሐዘን የገባው ቢሆንም፤ በሕይወት ሳሉ ለኢትዮጵያና ለግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስላሳዩት ወዳጅነትና ዘላቂ ግንኙነት "በኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት ስም ልንዘክራቸው እንወዳለን" ብሏል።

አክሎም፤ ንግሥት ኤልሳቤጥና አፄ ኃይለ ሥላሴ እርስ በርሳቸው የሚተማመኑና አንዳቸው ላንዳቸው አገር ሕዝብ ደህንነት ተጨናቂዎች እንደንበሩም አመላክቷል።
የንግሥት ኤልሳቤጥን የኢትዮጵያ ጉዞ አስመልክቶም "ንግሥት ኤልሳቤጥ ኢትዮጵያን የጎበኙት አፄ ኃይለ ሥላሴን እጅ ለመንሳት፣ የምንወደውን ሕዝባችንን በዓይናቸው ለማየትና ለመጠየቅ እንዲሁም ውብና ለምለም አገራችንን ለመጎብኘት ነበር" ብሏል።

የዘውድ ምክር ቤቱ መግለጫ " በሁለተኛው የኢጣሊያን ወረራ ጊዜ የንግሥት ኤልሳቤጥ አባት ንጉሥ አፄ ጊዮርጊስ 6ኛው ለአፄ ኃይለ ሥላሴ መሸሸግያ ቦታ እንዲይዙ በመፍቀድ ኢትዮጵያን ጭካኔ ከተሞላው የአምስት አመት የኢጣልያን ይዞታ ነፃ እንድናወጣና ሉዓላዊነታችንን ለሕዝባችን መልሰን እንድናስረክብ የተሰናዳንበትን ሁኔታ አመቻችተዋል" ሲልም የአገረ እንግሊዝና ኢትዮጵያ ወዳጅነት ከሉዓላዊነትና ሙሉዕ ነፃነት ጋር የተቆራኘ ስለመሆኑ ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ልዑል ኤርሚያስ ሣህለ ሥላሴ ኃይለ ሥላሴ የ1967 መስከረም 2 መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ላይ ግድያ በመፈፀሙ ሳቢያ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ላልቻሉ ንጉሣዊ ቤተሰቦች ንግሥቲቱ ድጋፍ በማድረግ ዘላቂ የቤተሰብ ጓደኛና ባውለታ መሆናቸውን እንዳስመሰከሩ ጠቅሰዋል።
አያይዘውም "እኔ በግሌ የንግሥቲቱ ደግትና ቸርነት ተካፋይ ስለነበርኩህ በቅርበት ንግሥቲቱና የብሪታንያ ሕዝብ ለኢትዮጵያውያን ሰለሞናዊ የዘር ሐረግ ተወላጅ ዘመዶቻቸው አለኝታና ሰብሳቢም ጭምር እንደነበሩ ለመገንዘብ ችያለሁ" ብለዋል።
የዘውድ ምክር ቤቱ ፕሬዚደንት፤ ንጉሥ ቻርልስ ሳልሳዊ ንግሥት ኤልሳቤጥ ከኢትዮጵያ ጋር ስለነበራቸው ጥልቅ ግንኙነት ጠንቅቀው እንደሚያውቁ አመላክተው "እኛም የተወደዱ እናታቸውን ሲያጡ እንደ ቤተሰብ የሐዘናቸው ተካፋይ ነን" ሲል በምክር ቤቱ ስም የሐዘን ተጋሪነታቸውን ገልጠዋል።
በመጨረሻም "እግዚአብሔር የዳግማዊት ኤልሳቤጥን ነፍስ ይማርልን። ወደ ፈጣሪዎ ስንሸኝዎት ሐዘናችንን የምንገልጸው በዕንባ ነው። ረጅም ዕድሜ ለንጉሥ ቻርልስ 3ኛው ከመልካም ምኞትና ፀሎት ጋር እንመኛለን። እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ለዘላለም ይባርክ" ብለዋል።

