ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን አምስት ሚኒስትሪያዊ ኃላፊነቶችን ደርበው ይዘው እንደነበር ገለጡ።
ስኮት ሞሪሰን ከማርች 2020 እስክ ሜይ 2021 በጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ላይ የጤና፣ ፋይናንስ፣የአገር ውስጥ ጉዳዮች፣ በጅሮንድ፣ ኢነርጂና ሃብቶች ሚኒስትርም ነበሩ።
ትናንት ሰኞ የአውስትራሊያ ጠቅላይ እንደራሴ ስኮት ሞሪሰን ተጨማሪ ሚኒስትሪያዊ ኃላፊነቶችን ቃለ መሐላ ፈፅመው ይዘው እንደነበር ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን የቀድሞው መንግሥት ምስጢራዊና ፓርላማውን ባሳሳተ መልኩ ይመራ እንደነበር ተናግረዋል።
የፋይናንስ፣ በጅሮንድና የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትሮች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥራ ኃላፊነቶቻቸውን ደርበው መያዛቸውን እንደማያውቁ ተናግረዋል።

Prime Minister Anthony Albanese. Credit: Brook Mitchell/Getty Images
የቀድሞዋ የሞሪሰን አገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ካረን አንድሩስ ሚኒስትራዊ ኃላፊነታቸው በስኮት ሞሪሰን ተይዞ እንደነበር ያወቁት በዚህ ሳምንት ከሚዲያ ሪፖርት እንደሆነ ጠቅሰው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ከኩክ ምክር ቤት አባልነታቸው እንዲለቁ ጥሪ አድርገዋል።
አክለውም፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ድርጊት ዲሞክራሲን እንደማይታደግና ለአውስትራሊያ ሕዝብም እንደማይበጅ ተናግረዋል።

Former Minister for Department of Home Affairs Karen Andrews. Credit: Tracey Nearmy/Getty Images
በርካታ የሞሪሰን ካቢኔ አባላት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አምስት ተጨማሪ ሚኒስትሪያዊ ስልጣኖችን ደርበው መዛቸውን ገና አሁን ስለመስማታቸው እየተናገሩ ነው።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የሚኒስትሮችን የሥራ ኃላፊነት ደርበው በመያዛቸው ቅር ያሰኟቸው ካሉ 'ይቅርታ' ብለዋል።
ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ የስኮት ሞሪሰን ድርጊት 'ዲሞክራሲን የሚያጎድፍ ነው' በማለት ሕጋዊ ምክር መጠየቃቸውንና ድርጊታቸው ሕጋዊ እርምጃን የሚያስወስድ መሆኑንና አለመሆኑን ለመለየት በሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ ከፌዴራል መንግሥቱ የሕግ አማካሪ ሕጋዊ ማብራሪያ እንደሚሰጣቸው ገልጠዋል።