የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ረቡዕ የካቲት 8 ቀን 2015 ባወጣችው መግለጫ በቤተ ክርስቲያኒቱ መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት መፈታቱን አስታወቀች።
መግለጫው "በዛሬው ዕለት የቤተ ክርስቲያን ጸሎቷ፣ ሐዘኗና ጩኸቷ ተሰምቶ ወደ ነበረችበት ልዕልናዋና አንድነቷ ተመልሳለች። ይህ አንድነቷና ልዕልናዋ እስከ ዓለም ፍፃሜ ተጠብቆ ይኖራል" ብሏል።
አያይዞም፤ በችግሩ አፈታት ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፖለቲካዊ ችግሩን በፖለቲካዊ መንገድ መፍታታቸውን ጠቅሶ፤ የቤት ክርስቲያን ችግር በቀኖናና በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት እንዲፈታ ታላቅ አስተዋፅዖ ማበረከታቸውን በመግለጥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከልብ ማመስገኗን አመላክቷል።
በማከልም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ "አሁን ችግሯ ተፈቷል ወደፊትም የቤተ ክርስቲያን ሉዓላዊነትና አንድነቷ ተጠብቆ ሙሽራው ክርስቶስ እስከሚመጣ በአንድነቷና በሉዓላዊነቷ ትኖራች" ማለታቸውን አንስቶ ቀደም ሲልም 'ቤተ ክርስቲያኒቱ አገር ናት' በማለት ክብሯን ሲገልጡ እንደቆዩ ሁሉ አሁንም ክብሯን ስለገለጡ "ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በድጋሚ ታመሰግናለች" ብሏል።

Ethiopian Prime Minister Abiy Ahmed (L) and Patriarch of the Ethiopian Orthodox Church Abune Matias (R). Credit: EPO
መግለጫው አያይዞም "ከዚህ በኋላ ከወንድሞቻችን ጋር በአንድነት ሆነ በቅዱስ ፓትሪያርካችን እየተመራን ሶኖዶሳዊ አንድነታችን አፅንተን የቤተክርስቲያንን መከራ መከራችን፣ ደስታዋን ደስታችን አድርገን አገልግሎቷን ለማጠናከርና የምዕመናን ጥያቄ በተገቢው ለመመለስ ተግተን የምንሠራ ይሆናል" ብሏል።
የቤተ ክርስቲያን ሶኖዶሳዊ አንድነት አይደፈርም በማለት ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች፣ የአካልና ስነ ልቦናዊ ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆቿን አስተባበራ የምታፅናና የምትደግፍ መሆኗም ተገልጧል።