የዘንድሮው የፊፋ የሴቶች የዓለም ዋንጫ ባለቤት ማን ይሆናል?

በአውስትራሊያና ኒውዚላንድ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚስተናገደው የፊፋ የሴቶች ዓለም ዋንጫ የፊታችን ሐሙስ ጁላይ 20 / ሐምሌ 13 ይጀምራል። ግጥሚያዎቹን እንደምን መመልከት እንደሚችሉ እነሆ።

Matildas.jpg

All eyes will be on Australia's Matildas during the FIFA Women's World Cup. Credit: Getty / Cameron Spencer

አንኳሮች
  • አውስትራሊያ 35 ኒውዚላንድ 29 ግጥሚያዎችን ያስተናግዳሉ
  • 15 ግጥሚያዎች በነፃ የቴሌቪዥን አገልግሎቶች ይሰራጫሉ
  • ሶስት የአፍሪካ አገራት በተወዳዳሪነት ይቀርባሉ
የፊፋ የሴቶች ዓለም ዋንጫ አፍቃሪዎች በእግር ኳስና አገር ፍቅር ስሜት ተመልተው የውድድሩን ጅማሮ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።

የውድድሩ መክፈቻ ሐሙስ ጁላይ 20 / ሐምሌ 13 ሲሆን ኦገስት 20 / እሑድ ነሐሴ 14 ይፈፀማል።

በመክፈቻው ዕለት ኒውዝላንድና ኖርዌይ የመጀመሪያውን ግጥሚያ የሚያካሂዱ ሲሆን፤ ከሰዓታት በኋላ አውስትራሊያና አየርላንድ ይጋጠማሉ።

የአፍሪካውያኑን ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካና ዛምቢያን ጨምሮ 32 አገራት ለዋንጫው ተሰላፊ ሲሆኑ፤ የሩብ፣ የግማሽ፣ የሶስተኛ ደረጃና የፍፃሜ ግጥሚያዎች ይካሔዳሉ።

አውስትራሊያ 35 ግጥሚያዎችን በአምስት ከተሞች የምታካሂድ ሲሆን፤ ኒውዝላንድ 29 ጨዋታዎችን በአራት ከተሞች ታከናውናለች።

የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ በዓለም የመጀመሪያው በአያሌ ታዳሚዎች ተመልካችነት ያላቸው ግጥሚያዎች እንደሚታዩበት ይጠበቃል። የቲኬት ሽያጮች በሚያስገርም መልኩ የተከናወኑ መሆናቸውን ፊፋ ገልጧል።

የፊፋ የሴቶች ዓለም ዋንጫን አውስትራሊያ ውስጥ እንደምን መመልከት እንደሚችሉ

የአውስትራሊያና ኒውዝላንድ ነዋሪዎች ቲኬቶችን በመግዛት በአካል ተገኝተው መመልከት ይችላሉ። እስከዛሬዋ ዕለት ድረስ ለተወሰኑ ግጥሚያዎች የሚሆኑ ቲኬቶች በሽያጭ ላይ ይገኛሉ።

ሲድኒና ሜልበርን በትላልቅ የቴሌቪዥን መስኮቶች ግጥሚያዎችን በዋነኛ አደባባዮች ለሕዝብ ያሰራጫሉ። ሌሎች ከተሞችም ምናልባት ለሕዝብ የአደባባይ ስርጭት እንደሚያደርጉ ሊያስታውቁ ይችላሉ።

ኦፕተስ ስፖርት - ሁሉንም ግጥሚያዎች በቀጥታና በጥያቄ የሚያሰራጭ ሲሆን ኧፕ ዳውንሎድ ማድረግንና ምዝገባ መፈፀምንም ይጠይቃል።

ቻናል 7 ቅንጭብና ድጋሚ ጨዋታዎችን፤ እንዲሁም 15 የቀጥታ ግጥሚያዎችን በነፃ ያሰራጫል።

የፊፋ የሴቶች ዓለም ዋንጫ አሸናፊነት ታሳቢዎች እነማን ናቸው?

በፊፋ ደረጃ ምደባ መሠረት ከዓለም 10 ምርጥ ቡድናቱ በታሳቢነት ይነሳሉ። በአንደኛ ደረጃ ላይ የምትገኘዋና የአራት ጊዜ አሸናፊዋ ዩናይትድ ስቴትስ ቡድን ቀዳሚ ተጠቃሽ ስትሆን፤ ጀርመን፣ እንግሊዝ፣ ብራዚል፣ ስዊድን፣ ፈረንሳይ፣ ስፔይን፣ ካናዳ፣ ኔዘርላንድስና አውስትራሊያ ተካትተው ይገኛሉ።

ይሁንና የአምና ሻምፒዮናነትና ከአራት ዓመት በፊት የዋንጫ ባለቤትነት ደረጃ ሁሌም ለድል የሚያበቃ ሬኮርድ አይሆንም።

በዓለም የሴቶች እግር ኳስ ደረጃ ምደባ 26ኛነትን ይዛ የምትገኘው ጥምር አዘጋጇ ኒውዝላንድ ግጥሚዎቹ በከተሞቿ ላይ ስለሚካሔዱ በሕዝብ ድጋፍ ከፍ ላለ ደረጃ እንደምትበቃ ታስባለች።

የዘንድሮው የአውስትራሊያ እግር ኳስ ቡድን ማቲልዳስ ከመቼው ጊዜ በበለጠ አካላዊ ብቃት፣ ስነ ልቦናዊ ዝግጅትና የእግር ኳስ ጥበብ ክህሎት ያላቸውን ወጣት ተጫዋች በማቀፏ ለዋንጫ ባለቤትነት ያላት ተስፋ በእጅጉ የላቀ ስለ መሆኑ በአገር ውስጥ የስፖርት ሳይንቲስቶች እየተነገረ ነው።

የማቲልዳስ ቡድን "ወርቃማው ትውልድ" የሚል ተቀፅላም ተሰጥቷታል።

ከአፍሪካ ሶስቱ ተወዳዳሪ ቡድኖች ውስጥ የናይጄሪያ ሴቶች ከፍ ያለ ውጤት፣ ብርቱ ተፎካካሪነትና የላቀ የእግር ኳስ ክህሎትን ያሳያሉ ተብሎ ይጠበቃል።


Share

Published

By NACA, Kassahun Seboqa Negewo
Source: SBS

Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service