በሳይክሎን ፍሬዲ በተጠቃችው ማላዊ የ190 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፤ ቁጥራቸው በቅጡ ያልታወቁ ሰዎች ቆስለዋል፤ የደረሱበት ሳይታወቅ ቀርቷል።
በአጎራባቺቱ ሞዛምቢክ ውስጥ ተጨማሪ 20 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
የማላዊ መንግሥት እንዳስታወቀው 60,000 ያህል ዜጎች በማዕበሉ ለጉዳት የተዳረጉ ሲሆን፤ 19 ሺህ ቤት አልባ ሆነዋል።
ድጎማ
የአውስትራሊያ ማኅበራዊ አገልግሎት ምክር ቤት በመጪው በጀት አውስትራሊያውያን ከኑሮ ውድነት ጋር እየታገሉ ባሉበት ሁኔታ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሰዎች መደጎሚያ ቅድሚያ ትኩረት እንዲሰጥ አሳሰበ።
የማኅበራዊ አገልግሎት ምክር ቤቱ በአሁኑ ወቅት በቀን $48 ለሚያገኙ የሥራ አጥነት ድጎማ ተቀባዮች ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተያይዞ ድጎማቸው ወደ $76 በቀን ከፍ እንዲል ጥሪ አቅርቧል።
አክሎም፤ መንግሥት የዘንድሮ በጀቱን ይበልጡን አካታችና ለረጅም ጊዜያት የሚዘልቅ መሠረታዊ የማኅበራዊ አገልግሎቶች ላይ እንዲያውል አሳስቧል።
የአውስትራሊያ ማኅበራዊ ምክር ቤት አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ካሳንድራ ጎልዲ፤ የአውስትራሊያ የሥራ አጥነት ድጎማ ከምጣኔ ሃብት ትብብርና ልማት አባል አገራት ውስጥ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።