ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን የመጀመሪያ ጊዜ ቤት ገዢዎች ከጡረታ አበል ተቀማጫቸው ላይ 40 ፐርሰንት - እስከ $50,000 ወጪ ማድረግ እንዲችሉ የሚፈቅደው የፓርቲያቸው የመኖሪያ ቤት ፖሊሲ የቤት ዋጋ ንረትን አያስከትልም ሲሉ እየተከራከሩ ነው።
የጡረታ አበል ሚኒስትር ጄን ሂዩም ግና ዛሬ ጠዋት በሰጡት መግለጫ ፖሊሲው የአጭር ጊዜ የቤቶች ዋጋ ንረትን ሊያስከትል እንደሚችል አምነዋል።
ይሁንና አቶ ሞሪሰን በዕድሜ የገፉ አውስትራሊያውያን ትላልቅ ቤቶቻቸውን ሸጠው ከሽያጩ እስከ $300,000 ወደ ጡረታ አበላቸው እንዲጨምሩ የሚፈቅደው ፖሊሲ የቤቶች የዋጋ ንረት እንዳያሻቅብ ይረዳል ሲሉ ተከራክረዋል።
አቶ ሞሪሰን የመኖሪያ ቤት ፖሊሲያቸው የገበያ ሁኔታ አመላካች ሞዴል ተሠርቶለት እንደሁና ሞዴሉንም ይፋ ያደርጉ እንደሁ ተጠይቀው ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
የምጣኔ ሃብት ተጠባቢዎችና ሌበር ፓርቲ ፖሊሲው የወጣቶችን ቀልብ ለመሳብ የታቀደ የመጨረሻ ደቂቃ ሙከራ እንጂ የቤት ችግርን የሚፈታ አይደለም። ከቶውንም ተቀማጭ የጡረታ አበላቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳደር ነው በሚል ትችቶችን ሰንዝረዋል።
የግሪንስ የምርጫ ዘመቻ
የአውስትራሊያ ግሪንስ ፓርቲ ዛሬ ሰኞ ምሽት የ173 ቢሊየን ዶላርስ ይፋ የምርጫ ዘመቻውን ይከፍታል።
የግሪንስ ፓርቲ ቅዳሜ ሜይ 21 / ግንቦት 13 በሚካሔደው አገራዊ ምርጫ የስልጣን ሚዛንን መጨበጥ ከቻለ ሰባት ቁልፍ ፖሊሲዎቹን ይዞ ከሌበር ፓርቲ ጋር ለመደራደር ውጥን መያዙን የፓርቲው መሪ አዳም ባንድት አስታውቀዋል።
በግሪንስ የመደራደሪያ ዝርዝር ውስጥ የጥርስና የአዕምሮ ጤና ሜዲኬይር ውስጥ እንዲታከል፣ አዲስ የጋዝና የደንጊያ ከሰል ማምረቻዎች እንዳይገነቡ፣ ዝቅተኛ ዋጋ ያላቸው ቤቶች እንዲገነቡ፣ ነፃ የሙዋዕለ ሕፃናት አገልግሎት፣ የተማሪዎች ዕዳ ስረዛ፣ የገቢ ድጎማ ጭማሪና የኡሉሩ መግለጫን ግብር ላይ ማዋል የሚሉ ሠፈረውበታል።