ለአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ የተገኙት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማት ውይይት አድርገዋል።
የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ እና የተመዱ ዋና ፀሐፊ ጉተሬዝ በዋናነት በአፍሪካ የሰላም እና የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ነው የተወያዩት።
ሙሳ ፋኪ ከውይይቱ በኋላ በማኅበራዊ በትዊተራቸው እንደገለፁት "በአፍሪካ በሁሉም ዘርፎች የተገኙ ድሎች በፀጥታ ችግሮች ምክንያት ወደ ኋላ የመመለስ ስጋት እንዳይኖርባቸው በጋራ ሊሠሩ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ውይይት አድርገናል" ብለዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ “የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራን ማፋጠን” በሚል መሪ ሐሳብ ቅዳሜና እሁድ የካቲት 11 እና 12 በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
በአሁኑ ወቅት በጉባኤው ለመሳተፍ የሀገራት መሪዎች አዲስ አበባ እየገቡ ነው።
በዛሬው ዕለትም የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ፣ የሌሴቶ ፕሬዚዳንት ሳም ማትኬኔ፣ የኬፕ ቬርዴ ፕሬዚዳንት ሆዜ ማሪያ ፔሬራ፣ የሞሪታኒያው ፕሬዚዳንት መሐመድ ኦውልድ ጋውዛኒ እና ሌሎችም መሪዎች አዲስ አበባ ገብተዋል።
[ደመቀ ከበደ ፡ ከአፍሪካ ሕብረት ፡ አዲስ አበባ]