የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ነሐሴ 12/2014 ባካሔደው ስብሰባ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝብ ክልል ስር የነበሩ 6 ዞኖችና 5 ልዩ ወረዳዎች በአንድ ክልል እንዲደራጁ 5 አምስት የተቃውሞ ድምፆች ገጥመውት በአብላጫ ድምፅ ይሁንታ አግኝቶ አልፏል።
በአንድ ክልል ስር እንዲደራጁ ይሁንታውን ያገኙት የወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ጌዴኦ እና ኮንሶ ዞኖችና የደራሼ፣ አማሮ፣ ቡርጂ፣ አሌ እና ባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች ናቸው።
የተቀሩት የሃድያ፣ ሃላባ፣ ከንባታና ጠንባሮ፣ ጉራጌ፣ ስልጤ ዞኖችና የም ልዩ ወረዳ በነባሩ ክልል እንዲቀጥል ተወስኗል።ተወስኗል።
ሕዝበ ውሳኔው በኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ አማካይነት የሚካሔድ ይሆናል።
***
በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ ላለው ግጭት ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት በቅርቡ የተቋቋመው የኢትዮጵያ የሰላም አማራጭ ዐቢይ ኮሚቴ የሰላም ምክረ ሃሳብ ሰነድ መፅደቁን ነሐሴ 11/ 2014 ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
የሰላም ምክረ ሃሳብ ሰነዱን ለማፅደቅ በተካሔደው ውይይት የመሠረተ ልማትና መሠረታዊ አገልግሎትችን በፍጥነት ለማስቀጠል፣ ከተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያበቁ ፖለቲካዊ ውይይቶችን በአጭር ጊዜ የሚያስጀምሩ ጉዳዮች ላይ መምከሩን አክሎ ገልጧል።
ቀደም ሲልም መንግሥት በራሱ ተሳሽነት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በየትኛውም ሥፍራና ጊዜ የሰላም ንግግር ለማድረግ ፈቃደኝነቱን የገለጠ መሆኑን አንስቷል።
ፅድቅ የተቸረው የሰላም ምክረ ሃሳብ ለአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ወኪል በአስቸኳይ እንዲቀርብ ውሳኔ ማሳለፉን፣ ውሳኔዎችንም ግብር ላይ የሚያውሉ ንዑስ ኮሚቴዎችና ተቋማት እንቅስቃሴዎቻቸውን ከወዲሁ እንዲያከናውኑና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የሰላም ምክረ ሃሳቡን የተመለከተ ማብራሪያ መሰጠቱ ተጠቅሷል።
ይሁንና ከመንግሥት ጋር የሰላም ንግግር እንዲያካሒድ የሚጠበቀው የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ግና የሰላም ኮሚቴው መግለጫ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ የማደናገሪያ ድርጊት እንደሁ በቲዊተር ገፃቸው ጠቅሰዋል።