የአውስትራሊያ ሥራ አጦች ቁጥር ካለፈው ወር በ 0.8 ፐርሰንት ከፍ በማለት 3.7 ፐርሰንት ደርሷል።
ለሥራ አጦች ቁጥር መጨመር አስባብ የሆነው 4,300 ሰዎች ሥራቸውን በማጣታቸውና የሠራተኞች ተሳትፎ በ 0.1 ፐርሰንት ዝቅ በማለቱ እንደሆነ የአውስትራሊያ ስታቲስቲክ ቢሮ አመልክቷል።
የፌዴራል በጅሮንድ ጂም ቻልመርስ፤ መንግሥት የሥራ አጥ ቁጥር እንደሚጨምር ይጠብቅ እንደነበረና ሆኖም ከዓለም አቀፍ የሥራ አጦች ቁጥር ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ይሁንና የተቃዋሚ ቡድን ምክትል መሪ ሱዛን ሊ ግና የሥራ አጥ ቁጥሩ በ 0.8 ፐርሰንት መጨመር "አሳሳቢ" ነው ብለውታል።
ቻይና - አውስትራሊያ
ቻይና ከዛሬ ጀምሮ የአውስትራሊያ ጣውላ ወደ አገሯ መግባቱን እንዲቀጥል መፍቀዷን አስታወቀች።
ቻይና ጣውላን ጨምሮ በሌሎችም የአውስትራሊያ የውጭ አቅርቦት ምርቶች ላይ ከ2020 አንስቶ ምጣኔ ሃብታዊ ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል።
ውሳኔው የአውስትራሊያን የንግድ ሚኒስትር ዶን ፋረልን ባለፈው ሳምንት የቤጂንግ ጉብኝት ተከትሎ መካሄዱ የሁለቱ አገራት ዲፖሎማሲያዊ ግ ንኙነቶች የመሻሻል ፍንጭ እንደሆነ ተተርጉሟል።
በአውስትራሊያ የቻይና አምባሳደር ሺያዖ ቺያን፤ የአገራቸው ጉምሩክ ባለስልጣናት የአውስትራሊያ ጣውላ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ቻይና እንዲዘልቅ መፈቀዱን ለአውስትራሊያ ግብርና ሚኒስቴር ማስታወቃቸውን ዛሬ ሐሙስ ሜይ 18 በኤምባሲያቸው ቅጥር ግቢ በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።