የአውስትራሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔኒ ዎንግ አውስትራሊያ ቀደም ሲል ለምዕራብ ኢየሩሳሌም በእሥራኤል መዲናነት ሰጥታ የነበረውን ዕውቅና መሻሯን አስታወቁ።
ሚኒስትሯ ኢየሩሳሌም ዋና ከተማነት ዕውቅና የሰላም ድርድሩ ከፍልስጥኤም ሕዝብ ጋር ዕልባት እስኪያገኝ ድረስ ይሁንታን አንደማያገኝ ገልጠዋል።
የቀድሞው የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚንኒስትር ስኮት ሞሪሰን የፕሬዚደንት ትራምፕን የ2017 የዩናይትድ ኤምባሲን ከቴል አቪቭ ወደ ምዕራብ ኢየሩሳሌም የማዞር ውሳኔ ተከትለው በዲሴምበር 2018 አውስትራሊያ ምዕራብ ኢየሩሳሌምን በእሥራኤል መዲናነት ዕውቅና እንድትቸር አድርገው ነበር።
ሴናተር ዎንግ በ2018 ሌበር ተቃዋሚ በነበረት ወቅት የኢየሩሳሌም ዋና ከተማነት በኢሥራኤልና ፍልስጥኤም መካከል በሰላማዊ ድርድር ዕልባት እስኪያገኝ ድረስ ለኢየሩሳሌም የመዲናነት ዕውቅና መስጠትን ተቃውሞ እንደነበርና አሁን በመንግሥትነት ውሳኔውን እንደሻረ አስታውቀዋል።
አቶ ሞሪሰንም ከአብዛኛው ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የተስፈነጠሩ እንደነበር ተናግረዋል።
አክለውም፤ መንግሥታቸው ለሁለት መንግሥታት መፍትሔ ኃላፊነት የተመላበት ድጋፉን በመቸር እንደሚቀጥልና የአውስትራሊያ ኤምባሲም ቴል አቪቭ ውስጥ እንደሚቆይ ገልጠዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዎንግ፤ አውስትራሊያ ሁሌም ሁነኛ የእሥራኤል ወዳጅ እንደሆነችና ለፍልስጥኤም ሕዝብም ረድኤትን ጨምሮ የማይናወጥ ድጋፍ እንዳላት አመላክተዋል።