የኢትዮጵያ መንግሥት ጥቅምት 7 ቀን 2015 የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር የአስቸኳይ ተኩስ አቁምና የሰብዓዊ ረድዔት ይቀጥል ጥሪን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ በኅብረቱ አማካኝነት ለሚካሔደው የሰላም ውይይት ዝግጁ ስለመሆኑ ገልጧል።
አያይዞም፤ መንግሥት የአገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን፣ የፌዴራል ተቋማትን፣ ታላላቅ መሠረተ ልማቶችንና በተለይም የአየር ክልልን የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ጠቁሟል።
አክሎም፤ እኒህን ዓላማዎቹን በአንድ በኩል እያስፈፀመ፤ በሌላ በኩል በአፍሪካ ኅብረት በኩል ለሚካሔደው የሰላም ውይይት ዝግጁነቱን አመላክቷል።
ሕዝብና ሠራተኞችም ከሕወሓት ወታደራዊ ተቋማት እንዲርቁ ሲልም አሳስቧል።
በማጠቃለያውም "በትግራይ ክልል የሚገኙ ዜጎቹን ደኅንነት ለመጠበቅ በሕግ የተሰጠውን ሕገ መንግሥታዊ ግዴታውን ለመወጣት የኢትዮጵያ መንግሥት ያለውን ዝግጁነት በዚህ አጋጣሚ ያረጋግጣል" ብሏል።