በሶሪያና ተርኪዬ በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ከ46 ሺ ያለፈ ሲሆን፤ ከቶውንም የሟቾች ቁጥር ሊንር እንደሚችል ይጠበቃል።
አያሌ ሰዎች እስካሁንም የደረሱበት ያልታወቀ ሲሆን፤ ከፍርስራሾች ስር ሆነው የድረሱልን ጥሪ የሚያሰሙ ድምፆችንም የድንገተኛ አደጋ ደራሽ ሠራተኞች እየሰሙ መሆኑ ተነግሯል።
ተርኪዬ ውስጥ በደረሰው አደጋ 264 ሺህ ያህል አፓርትመንቶች ወድመዋል።
ሶሪያ ውስጥ የአደጋው ሰለባ የሆኑ ሰዎች ጉዳይ አሳስቢ የሆነ መሆኑን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ያመለከተ ሲሆን፤ በሰሜናዊ ምዕራብ በኩል በመቶ ሺህዎች ለሚቆጠሩ እርዳታ ፈላጊዎች እገዛዎችን ለማድረስ እንዲችል የሶሪያ ባለስልጣናትን እየወተወተ መሆኑን ገልጧል።
ድምፅ ለፓርላማ
ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ ለነባር ዜጎች ድምፅ ለፓርላማ ሕዝበ ውሳኔ በወርኅ ኦክቶበር ወይም ዲሴምበር ሊካሔድ እንደሚችል ጠቆሙ።
አቶ አልባኒዚ ሕዝበ ውሳኔው ከፌዴሬሽን ምሥረታ 100 ዓመታት ወዲህ ይህ ወሳኝ መልካም ዕድል እንደሆነ አስገንዝበው፤ መሪዎች ዕድሉን በቀናነት ተመልክተው ድጋፋቸውን እንዲቸሩት ጥሪ አቅርበዋል።
ድምፅ ለፓርላማ ነባር ዜጎች በሆኑና ባልሆኑ ዜጎች መካከል ያሉትን ልዩነቶችን ማጥበቢያ፣ ዕርቅና ምክክር እንደሆነም አመላክተዋል።