የ37 ዓመቷ የኒውዚላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደን ከጠቅላይ ሚኒስትራዊ የሥራ ኃላፊነትቸውና ከፖለቲካው ዓለም እንደሚሰናበቱ ዛሬ ሐሙስ ጃኑዋሪ 19 / ጥር 11 አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ከሥራቸው ለመሰናበት የወሰኑት ለሚቀጥለው ምርጫ ለውድደር ለመቅረብና በቀጣይነትም ለመዝለቅ ውስጣቸው የቀረ ኃይል የሌለ በመሆኑና እንዲያ ባለ ሁኔታ መቀጠሉ "አገሪቱን መበደል" እንደሚሆን በመገንዘብ መሆኑን ገልጠዋል።
በታካይነትም ቀሪ ጊዜያቸውን ከቤተሰባቸው ጋር ለማሳለፍ መሻታቸውም ሌላኛው አስባብ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንኑ የማይቀለብሱትን ከሥልጣን የመልቀቅ ውሳኔያቸውን ዛሬ ጠዋት ለካቢኔያቸው ሲያሳውቁ አባላቱ በውሳኔያቸው ግር መሰኘታቸውንና የተወሰኑ የቤተሰባቸው አባላት በሥራቸው እንዲቀጥሉ ያበረታቷቸው መሆኑን ገልጠዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው የአገልግሎት ጊዜያት የወጠኑትን ግብር ላይ በማዋላቸው "ፀፀቶች የሉኝም፤ የተቻለኝን ያህል መከወኔን አውቃለሁና" ብለዋል።
እንደምን ሊታሰቡ እንደሚሹ ከጋዜጠኞች ተጠይቀው ሲመልሱ "መታወስ የምሻው ሁሌም መልካም ለመሆን እንደሚጥር ሰው ነው" ሲሉ መልሰዋል።
ለቤተሰባቸው ያላቸውን መልዕክት ሲያስተላልፉም፤
በቀዳሚነት ለአራት ዓመት ሴት ልጃቸው ኔቭ "ኔቭ፤ በዚህ ዓመት ትምህርት ቤት ስትጀምሪ እናትሽ እዚያ ለመገኘት ትሻለች"
ለፍቅረኛቸው "ክላርክ፤ ጋብቻችንን እንፈፅም" ብለዋል።
የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ በቲዊተር ገፃቸው ለኒውዚላንዷ ጠቅላይ ሚኒስትር ያላቸውን የአመራር ክህሎት አድናቆትና ወዳጅነታቸውን አንስተው አመላክተዋል።
ከአያሌ አድናቂዎቻቸውም በርካታ የአድናቆትና መልካም ምኞት መልዕክቶች እየጎረፉላቸው ነው።