ከ 38 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የምርጫ ካርድ የወሰዱበት የዘንድሮው ምርጫ የመራጮች ድምፅ አሰጣጥ ሂደት ያለ ፀጥታ ስጋት ይከናወናል ብሎ ቦርዱ እንደሚያምን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሯ ሶልያና ሽመልስ ዓርብ ሰኔ 11, 2013 በዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ተናግረዋል።
ሶልያና በእስካሁን የቦርዱ ምልከታና ከፀጥታ ተቋማት ካገኙት መረጃ እንደተገነዘቡት የምርጫ ሂደቱን ሊያውክ የሚችል ጉልህ የፀጥታ ችግር ሊያጋጥም እንደማይችል እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል።
አጠቃላይ የምርጫ ዝግጅቱ ከጥቃቅን ችግሮችና የመቀናጀት ክፍተቶች በስተቀር በቦርዱ ዕቅድ መሰረት እየተከወነ ነውም ብለዋል።
የድምጽ መስጫ ቁሳቁሶችን የማሸጉና ከማዕከል ወደ ምርጫ ጣቢያዎች የማንቀሳቀስ ሥራ ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ መከናወኑን የገለፁት ሶልያና ቦርዱ አስቸጋሪ በሚባሉት እንደ አኮቦ ምርጫ ጣቢያ ያሉ ቦታዎች ጭምር የምርጫ ቁሳቁስ ማድረስ መቻሉን ነው የገለጹት። ቀሪ የምርጫ ቁሳቁስ ስርጭት የሚካሄድባቸው በደቡብ ክልል 4 የምርጫ ክልሎች እንዲሁም በአፋር ክልል አንድ የምርጫ ክልል የአየር ትራንስፖርት በመጠቀም የሚከናወን ይሆናል ሲሉ አብራርተዋል።
በተለይም የድምጽ መስጫ ወረቀቶችንና ውጤት ማሳወቂያ ቅፆችን ወደ ምርጫ ክልል በማድረሱ ስራ ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ አየር ኃይል ላደረጉላቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል።
ቦርዱ በገለልተኝነትና ባለው ውስን የሰው ኃይል ምርጫን ያህል ትልቅ ጉዳይ እየከወነ ነው ያሉት ሶልያና ከሚመለከታቸው አካላት የሚፈልገውን ድጋፍና ትብብር ለማግኘትና ነፃነቱን ለማስከበር በተቻለው አቅም ሚዛኑን ጠብቆ ለመንቀሳቀስ ሞክሯል ብለዋል።
በዚህም ምርጫው በታቀደለት መልኩ እንዲፈፀም ሌት ተቀን እየሰራን ነው ያሉ ሲሆን የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ፣ ቆጠራውና ውጤት አገላለፁ በጥራት እንዲከናወን ተዘጋጅተናል ብለዋል። የድምፅ ድመራና ውጤት ገለፃው በፍጥነት ይከናወናል ሲሉም ተናግረዋል።
በድምፅ አሰጣጥም ይሁን በውጤት ገለፃ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የሀሰተኛ መረጃዎችን ለማጣራትና ለመከላከል አስራ አንድ አባላት ያሉት የሶሻል ሚዲያና መደበኛ ሚዲያ ፍተሻ ቡድን አቋቁመናል ፣ ከፌስቡክ ካምፓኒ ጋርም በትብብር እንሰራለን ብለዋል።
[ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ ]