በተለይም የጋራ የጉምሩክ ሥርዓትና ወጥ የታሪፍ አስተዳደር በአሕጉሪቷ ለመተግበር ትኩረት እንዲደረግበት፣ የእርስ በርስ የንግድ ግንኙነትን የሚያቀጭጩ አሰራሮች መሻሻል እንደሚገባቸውና የተሳለጠ የንግድ ሥርዓት ለመፍጠር ሀገራት ትኩረት እንዲሰጡ የመከረ ሲሆን፤ በአፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ የተከሰቱ የድርቅና ረሃብ ጉዳቶችን እንዲሁም በዩክሬንና በሩስያ ጦርነት ምክንያት አደጋ ላይ የወደቀውን የአሕጉሪቱን የምግብ ዋስትና ችግር በተመለከተ ምክክር አድርጓል፡፡
የአፍሪካ የ2063 አጀንዳ አፈጻጸም፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የተሻለች አፍሪካን ለመገንባት የተቀመጠውን የረዥም ጊዜ ዕቅድ አፈጻጸም ላይም የኮሚሽኑን ሥራዎች ሪፖርት ተመልክቷል፡፡
• በጉባኤው እነማን ተገኙ?
ዓመታዊው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ትናንት እና ዛሬ ተካዷል፤ እንደተለመደው መዲናዋ በሽርጉድ ተጠምዳ፣ ነዋሪዎችና አሽከርካሪዎች “በእንግዶች” ሰበብ ሲዋከቡ ሰንብተዋል፡፡
በመረጃዎች መሰረት 35 የሀገራት መሪዎች (ፕሬዚደንቶች እና አራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች)፣ 11 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ 13 ቀዳማዊ እመቤቶችና 10 የዓለም አቀፍ ድርጅት ኃላፊዎች አዲስ አበባ ጉባኤውን ታድመዋል፡፡
በጥቅሉ 852 ጋዜጠኞች (332ቱ የሀገር ውስጥ እንዲሁም 70ዎቹ ተቀማጭነታችውን ኢትዮጵያ ያደረጉ የውጭ ሀገራት መገናኛ ብዙኃን የዜና ወኪሎች) 450ዎቹ ደግሞ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ የውጭ ሀገራት መገናኛ ብዙኃን ጊዜያዊ የዜና ወኪሎች ጉበኤውን ለመዘገብ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ፈቃድ አግኝተው ጉባኤውን ዘግበዋል፡፡
“የአፍሪካ ሕብረት የአደጋ አስተዳደር አሸናፊዎች ” በሚል መሪ ሃሳብ በአህጉሪቷ ለተከሰቱ አደጋዎች የሀገራትን ማለትም ኢትዮጵያን ጨምሮ ሞዛምቢክ፣ ናይጀሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዑጋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ቱኒዚያ፣ ማዳጋስካር፣
ኬኒያ፣ አንጎላ እና ግብጽ ምላሽ በሚያሳይ የፎቶ አውደ ርዕይ የተከፈተው ጉበኤ “የአፍሪካ አሕጉራዊ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራን ማፋጠን” በሚል መሪ ሀሳብ ነው የተካሄደው፡፡
ጉባኤው ከኹለት ዓመት በፊት ሥራ ላይ መዋል የጀመረው “አሕጉር-ዓቀፉ የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጠና ስምምነት ” አፈጻጸምና የደረሰበት ደረጃን በዋና አጀንዳነት በመያዝ በሀገራት መሪዎች የጎንዮሽ ግምገማና ውይይት ጭምር ተደርጎበታል፡፡
የአፍሪካ የነጻ ንግድ ቀጠና ስምምነት ሙሉ በሙሉ ሲተገበር ከ98 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ከድህነት ሊያላቅቅ እንደሚችል ሕብረቱ በይፋዊ መግለጫው ያስታወቀ ሲሆን በአሕጉሪቱ 30 ሚሊዮን ዜጐችን ከከፋ ድህነት እንዲሁም 68 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችን ደግሞ ከመካከለኛ ደረጃ ወደ ከፍ ያለ የሃብት ደረጃ ያሸጋግራቸዋል ብሏል። ይህ የነጻ ንግድ ቀጠናው ስምምነት ትግበራ ሂደት ሲፋጠንም፣ በፈረንጆቹ 2035 የአህጉሪቱን ገቢ በ450 ቢሊዮን ዶላር ያሳድገዋል ሲልም አክሏል ኅብረቱ፡፡
ከመሪዎቹ ጉባኤ ቀደም ብሎ 42ኛው የኅብረቱ ሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ጉባኤ መካሄዱ ይታወሳል።
• በጉባኤው መሪዎች ምን አሉ?
በጉባኤው መክፈቻ ንግግሮች መሪዎችና የተቋማት ኃላፊዎች ሰራናቸው ያሉትንና ትኩረት ያሻቸዋል ያሏቸውን ጉዳዮች ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ጉባኤ አፍሪካ የቡድን 20 አባል ሀገራት ሙሉ አባል ለመሆን ጥያቄ እንደታቀረብ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ያቀረበችው ጥያቄ በጥሩ ሂደት ላይ መሆኑን የጉዳዩ አስተባባሪና ስልጣናቸውን ለኮሞሮስ ፕሬዝደንት ያስረከቡት የቀድሞው የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርና የሴኔጋል ፕሬዝደንት ማኪ ሳል ገልጸዋል፡፡

Outgoing chairperson of the African Union (AU) and Senegal President Macky Sall (2nd R) hands the gavel to incoming Chairperson and Comoros President Azali Assoumani (2nd L) during the 36th Ordinary Session of the Assembly of the African Union (AU) at the African Union Headquarters in Addis Ababa on February 18, 2023. Credit: TONY KARUMBA/AFP via Getty Images
በአውሮፓ ሕብረት፣ የቡድን 7 አባል አገራት እና መሰል ስብሰባዎች ላይ ከአፍሪካ ጋር የትብብር ግንኙነቶች አንዲጠናከሩ የማድረግ ፍላጎት መኖሩን ጠቁመዋል።
ማኪሳል የአፍሪካ ህብረትን በሊቀመንበርነት በመሩበት ጊዜ አሕጉሪቷ ከዓለም መንግስታት ጋር ያላትን ግንኙነት በማጠናከር በኩል የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸው በዓለም ምጣኔ ሃብትና የፋይናንስ ስርአት ፍትሃዊነት ጉዳይ እንዲሁም የቡድን 20 አባል ሀገራት ሙሉ አባል ለመሆን አፍሪካ ያቀረበችው ጥያቄ በመልካም ሂደት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት ሩስያ፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ቻይናን ጨምሮ ከ20 በላይ የቡድን 20 አባል አገራት ድጋፋቸውን መግለጻቸውንም ያብራሩት ማኪሳል ሌሎች አባል ሀገራትም ይህንን ድጋፍ በመቀላቀል በቀጣይ በህንድ በሚካሄደው የአባል ሀገራቱ ስብሰባ ላይ አፍሪካ የቡድን 20 አባልነት ዕውን ይሆናል የሚል ግምት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ማኪ ሳል በአሕጉሪቱ የምጣኔ ሃብት መነቃቃትን ለማምጣት የተፈጥሮ ሃብትን በመጠቀም ለዓለም ገበያ በተወዳዳሪ ዋጋ ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ፤ በተለይም በአሕጉሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ማግኘት ላልቻሉ ከ600 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የሃይል አቅርቦት ዕውን ማድረግም ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ምጣኔ ሃብት የሚያስፈልገውን ያህል የፋይናንስ አቅርቦትና ድጋፍ እያገኘ ባለመሆኑ የፋይናንስ ድጋፍና አማራጭን ማጠናከር እንደሚገባ ያሳሰቡት የቀድሞው የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ለአዲሱ ተመራጭና የ2023 የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር የኮሞሮስ ፕሬዝዳንት አዛሊ አሱማኒ ሊቀመንበርነቱን በይፋ አስረክበዋል።
ሌላኛው የጉባኤው ተናጋሪ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃመት ደግሞ አፍሪካን ከተባበሩት መንግስታት ደርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ማግለል ኢፍትሃዊነት መሆኑን አትኩረውበታል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት ሁሉንም አባል ሀገራት ማዕከል ያደረገና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ እንዲሆን እየሰራን እንገኛለን ሲሉ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃመት ጉባኤውን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል። በዓለም የሚታየውን የተዛባ አመለካከትና የመንግስታት አስተዳደር ለማስተካከል አሁንም ድምጻችንን ማሰማት መቀጠል እንደሚገባ የገለጹት ሙሳ ፋኪ አፍሪካን ከተባበሩት መንግስታት ደርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ማግለል ኢፍትሃዊ ውሳኔ ነው ብለዋል፡፡

Minasse Wondimu Hailu/Anadolu Agency/Getty Images Credit: Minasse Wondimu Hailu/Anadolu Agency/Getty Images
ሙሳ ፋኪ ሽብርተኝነትና ከምርጫ ውጭ ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ ጥረትና የአየር ጸባይ ለውጥ አሁንም የአጉሪቱ ችግሮች ሆነው መቀጠላቸውን የተናገሩ ሲሆን በአህጉሪቱ ህገ መንግስትን በጣሰ መልኩ ስልጣን የሚወጡ ኃይሎች ላይ የሚጣሉ ማዕቀቦች ውጤት ከማስገኘት ይልቅ ህዝብን ለችግር መዳረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡ በመሆኑም ማዕቀቡ የሀገራትን ኢኮኖሚ የሚያንኮታኩትና ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆኑን በመገንዘብ አማራጭ የመፍትሄ እርምጃ ማስቀመጥ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ሙሳ ፋኪ “አፍሪካን በ2030 የጥይት ድምጽ የማይሰማባት አሕጉር” ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ግባቸውን እንዲመቱ ሕብረቱ ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ እየተንቀሳቀሰ ነው ያሉ ሲሆን “የተደቀኑ ችግሮችንና ይዘዋቸው ሊመጡ የሚችሉ ፈተናዎችን ቀድመን በመገንዘብ በጋራ ልናልፋቸው ይገባል” ብለዋል።
አክለውም የአፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ዕድገት ባለፉት ሶስት ዓመታት በገጠሙት ዘርፈ ብዙ ችግሮች በነበረበት መቀጠል አልቻለም ያሉት ሙሳ ፋኪ “የዋጋ ግሽበቱ ከሚጠበቀው በላይ ማሻቀብ፣ የነዳጅ ዋጋ መጨመርና ግጭት የአሕጉሪቱ ሳንካዎች ሆነው ቀጥለዋል፤ ይህ ደግሞ የሀገራትን ኢኮኖሚ የሚያንኮታኩትና አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር መሆኑን በመገንዘብ አማራጭ የመፍትሄ እርምጃ ማስቀመጥ ይገባል” ብለዋል፡፡
የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ “የአፍሪካን ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት” ዕውን ለማድረግ መሰረተ ልማት፣ ኢነርጂኒና ዲጂታላይዜሽንን ማፋጠን ዋነኞቹ መሰረቶች ሲሆኑ ይህን ራዕይ ማሳካት የሚቻለው በመሪዎች ቁርጠኝነት ብቻ ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው እንደአምናው ንግግራቸው ሁሉ ዘንድሮም “በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ መቀመጫ ይገባታል”፤ እንዲሁም “ለአፍሪካ ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ የሚያቀርብላት የአፍሪካ ህብረት አሕጉራዊ ሚዲያ ያስፈልጋል ብለዋል ለጉባኤው ታዳሚዎች፡፡
ዶ/ር ዐቢይ “ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ በገጠማት ችግር ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የተሳሳተ መረጃ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሲያደርሱ ቆይተዋል” ያሉ ሲሆን ለአፍሪካ ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ የሚያቀርብላት የአፍሪካ ሕብረት አሕጉራዊ ሚዲያ መቋቋም ደግሞ መፍትሔ ነው ብለዋል፡፡

Ethiopian Prime Minister Abiy Ahmed gives an address at the opening of the 36th Ordinary Session of the Assembly of the African Union (AU) at the African Union Headquarters in Addis Ababa on February 18, 2023. Credit: TONY KARUMBA/AFP via Getty Images
ዶ/ር ዐቢይ “ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራና በበጋ መስኖ በምግብ ራሷን ለመቻል ውጤታማ ስራ ሰርታለች” ያሉ ሲሆን “ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ውጤታማ የአየር ንብረትን ለመቋቋም የሚያስችል ስራ ተሰርቷል። በምግብ ራሷን ለመቻል ባደረገችው ጥረት የበጋ የስንዴ መስኖ በመዝራት ከራሷ አልፋ ወደ ውጭ መላክ ጀምራለች” ሲሉ በሕብረቱ ጉባኤ ላይ ተናግረዋል፡፡
• የኮሞሮስ የአፍሪካ ሕብረት መሪነትን መረከብ
የ36ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ሌላው ጉዳይ ከ900 ሺህ በላይ ሕዝብ ያላት ትንሽየዋ ደሴት ኮሞሮስ የ2023 አፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበርነትን ከሴኔጋል በይፋ መረከብ ነው፡፡ በጉባኤው የኮሞሮስ ፕሬዝዳንት አዛሊ አሱማኒ በመጪዎቹ 12 ወራት የአፍሪካ ሕብረትን በሊቀ መንበርነት/አንዳንዶች ፐሬዝደንትነት ይሉታል/ እንድትመራ ከወቅቱ የሕብረቱ ሊቀ መንበር ከሴኔጋል ፕሬዝደንት ማኪ ሳል በይፋ ተረክባለች።
ታዲያ የደሴቲት ፕሬዝደንት አዛሊ አሱማኒ በይፋዊ የስልጣን መረካከቢያ ንግግራቸው “የአፍሪካ አገራትን የብደር ጫና ለማቃለል አበዳሪ አገራትና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የጋራ የብድር ማቅለያ ማዕቀፍ በማበጀት ሊሰሩ ይገባል” ብለዋል፡፡
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት የኮቪድ 19 ወረርሺኝ እና የዩክሬንና የራሽያ ጦርነት በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአፍሪካ ከባድ ተጽዕኖ ማሳደሩን የጠቆሙት አዛሊ ይህንንም ተከትሎ የአፍሪካ አጠቃላይ እድገት ከሦስት በመቶ እንዳይልቅ ማድረጉን በመጥቀስ በአንጻሩ የአህጉሪቱ የውልደት መጠን ከፍተኛ መሆኑ አሉታዊ ጫና አሳድሯል ብለዋል፡፡ በተለይም የአህጉሪቱን የማኅበራዊና መሰረተ-ልማት በተፈለገው ደረጃ እንዳያድግ በማድረግ 22 የሕብረቱ ሀገራት የብድር ጫና ውስጥ ስመሆናቸው የዓለም ባንክን መረጃ የጠቀሱት አዲሱ የሕብረቱ መሪ እነዚህ አገራት ዕዳቸውን ለመክፈል ስለሚያዳግታቸው የብድር ጫናውን ለማቃለል አበዳሪ
ሀገራትና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የጋራ የብድር ማቅለያ ማዕቀፍ ሊያዘጋጁላቸው ይገባል ብለዋል። “ምዕራባውያን ከወራት በፊት ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ማገገሚያ የሚውል 150 ቢሊየን ዩሮ ለመስጠት የገቡትን ቃል በመጠበቅ ገንዘቡን በፍጥነት መልቀቅ አለባቸው”ም ብለዋል።
“የዩክሬንና የሩስያ ጦርነት አፍሪካ ራሷን መቻል እንዳለባት አሳይቶናል” ያሉት አዛሊ ፤ በተለይም የግብርና ዘርፉን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው በአሕጉሪቱ የምጣኔ ኃብትና ጠንካራ የፖለቲካ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማሳደግ በእሳቸው የአመራር ዘመን ቅድሚያ የሚሰጠው ሥራ ይሆናል ብለዋል፡፡ በአፍሪካ ሀገራትና አጋር አካላት እንዲሁም ከሌሎች አቻ ተቋማት ጋር ያለውን ትብብር በማጠናከር አህጉሪቱን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሻገር በሊቀ-መንበርነት ጊዜያቸው የሚሰሩ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
• የተመድ ዋና ጸሐፊው አንቶኒዮ ጉተሬዝ - በጉባኤው
በጉባኤው የተገኙት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “አፍሪካ አፍሪካ እምቅ የሆነ የመልማት አቅም አላት። ይህን አቅም ለማልማትና ያሉባትን ችግሮች ለመፍታት በምታደርገው ጥረት የተባበሩት መንግስታት ድጋፍ ያደርጋል” ያሉ ሲሆን “ነጻ የንግድ ቀጠናን ማሳለጥ ለስራ እድል ፈጠራ ወሳኝ በመሆኑ አፍሪካ በ2060 ለያዘችው የግብ አጀንዳ ያላትን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ህዝቡ ያለበትን ችግር በመፍታት የተሻለ እድገት ማስመዝገብ ተገቢ ነው” ብለዋል፡፡ ጉተሬዝ “ለዚህ ግብ ስኬት ደግሞ አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እገዛ ማድረግ አለባቸው” ሲሉም አጽኦት ሰጥተዋል፡፡
የዓለም የፋይናንስ ስርዓት ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለአፍሪካና አጠቃላይ በማደግ ላይ ላሉ ሀhገሮች በሚጠቅም መልኩ መቃኘት ይኖርበታል ያሉት ዋና ጸሐፊው ዓለምን እየፈተነ ላለው የአየር ንብረት ለውጥ ችግርም ዕልባት ለማበጀት የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። ለዚህ ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካን የልማት እቅዶች በመደገፍ በአሕጉሪቱ ዘላቂ ሰላምና ቀጣይነት ያለው ዕድገት ዕውን እንዲሆን ድጋፉን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

United Nations (UN) Secretary-General Antonio Guterres gave an address during the 36th Ordinary Session of the Assembly of the African Union (AU) at the African Union Headquarters in Addis Ababa on February 18, 2023. Credit: TONY KARUMBA/AFP via Getty Images
ጉተሬዝ አፍሪካን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም አገራት በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ለመርዳት የሚውል 250 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ይፋ አድርገዋል፡፡ ድጋፉ በመንግሥታቱ ድርጅት ማዕከላዊ የእርዳታ ምላሽ ፈንድ አማካኝነት የተለቀቀ
መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ከ339 ሚሊየን በላይ ሰዎች ለችግር መጋለጣቸውን ዋና ጸሐፊው ጠቁመዋል። ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ25 በመቶ ብልጫ እንዳለው ጠቅሰዋል።
• የጎንዮሽ ውይይቶችና ምክክሮች
በሕብረቱ ጉባኤ የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝን ጨምሮ የሀገራት መሪዎችና የተለያዩ ተቋማት የጎንዮሽ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡
ፕሬዝደንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ፣ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና ምክትል ጠቅላይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በየፊናቸው የተለያዩ ሀገራትና ተቋማት መሪዎችን በቀጣናዊ እና የሁለትዮሽ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ማወያየታቸውን የመንግስት ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
እንደመረጃዎቹ ከአንቶኒዮ ጉተሬዝ፣ ከሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ፣ ከኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቲሼኬዲ፣ ከሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ፣ ከፕሬዝዳንት ኢቫሪስቴ ንዳዪሺሚዬ፣ ከአውሮፓ ሕብረት ተወካዩ ከቻርለስ ሚሼል፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር አኪንውሚ አድሲና፣ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ረዳት ዳይሬክተ ሜሪ ካትሪን እና ሌሎችም ጋር ተወያይተዋል፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጅቡቲው ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ ጋር ሆነውም አዲሱን የጅቡቲ ኤምባሲ መርቀው የከፈቱት በዚሁ የሕብረቱ ጉባኤ የጎንዮሽ ክንውን ነው፡፡
በአፍሪካ ሕብረት፣ የሴራሊዮን መንግስት እና በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ትብብር የተዘጋጀ የትምህርት ውይይትም ተከካሂዷል፡፡ በአፍሪካ ሕብረት እና በዩኒስኮ ትብብር ከ2016 እስከ 2025 ዓ.ም የአህጉሪቷን ፍትሐዊ የትምህርት ስርዓት ለማሻሻል እየተሰራ የሚገኘውን የፖሊሲ ሪፖርት አስመልክቶ ነው ውይይት የተካሄደው፡፡
በውይይቱም የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ሳኅለወርቅ ዘውዴ፣ የሴራሊዮን ፕሬዚደንት ጁሊዬስ ማዳ ባዮ፣ የዩኒስኮ ዋና ዳይሬክተር አውድረይ አዞውላይ እና የሌሎች አገራትም ተወካዮች ተሳትፈዋል። በውይይቱ ከ5 አፍሪካዊያን ህፃናት መካከል አንዱ ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆኑን የተነገረ ሲሆን ድህነትን በማሸነፍ የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ የትምህርት ጥራትና ፍትሕዊ ተደራሽነት እንዲኖር መስራት እንደሚገባ ተመክሮበታል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Ethiopia's President Sahle-Work Zewde. Credit: Minasse Wondimu Hailu/Anadolu Agency/Getty Images
በመሆኑም በሽታውን ለመከላከል ተጨማሪ የ15 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር የሚያስፈልግ በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትብብር እንዲያደረግ ጥሪ አቅርበዋል። ውይይቱን የታደመው እንደ ኢዜአ ዘገባ በዘንድሮው የአፍሪካ መሪዎች የወባ መከላከል ጥምረት ሽልማት መርሃ-ግብር ኢትዮጵያን
ጨምሮ ዴሞክራቲክ ኮንጎ፣ ሩዋንዳ፣ ጋና፣ ዛምቢያ፣ ታንዛኒያ እና ኬንያ በወባ በሽታ መከላከል ላይ ባከናወኑት ተግባር እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
በሌላ ውይይት የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተደራዳሪዎች ቡድንም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመጭው የኮፕ 28 ስብሰባ የአፍሪካን ፍላጎት የሚያንጸባርቅ ስትራቴጂ ላይ ምክክር አካሂዷል፡፡ የፓን አፍሪካ የአየር ንብረት ፍትህ አሊያንስ (PACJA)፣ ከመላው አፍሪካ የተውጣጡ ባለድርሻ አካላትን በመሰብሰብ ለኮፕ 28 ስትራቴጂ ነድፏል፡፡
በአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚሰሩ የተለያዩ ማኅበበራትና ግብረሰናይ ድርጆቱ የተሳተፉበት ምክክር፣ የአፍሪካን የአየር ንብረት አቋም የአፍሪካ ተደራዳሪ ቡድን መጭው የኮፕ 28 ስብሰባ ቁርጠኛ አቋም ይዞ እንደሚቀርብም ተመላክቷል፡፡
ተደራዳሪ ቡድኑ ባለፈው ዓመት በግብጽ በተካሄደው ኮፕ 27 ያስመዘገባቸውን ስኬቶች ለማጠናከር መወሰኑን ያስታወቀ ሲሆን፣ በኮፕ 28 ሰብሰባ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ከባድርሻ አካላት የሚያገኛቸውን ግብዓቶች እንደሚተቀም ገልጿል፡፡
በአየር ንብረት ለውጥ ድርድር ሂደት ውስጥ የአፍሪካ አጀንዳ እውን ለማድረግ፣ የአፍሪካ መንግሥታት የዓላማ አንድነትን ለማረጋገጥ በቴክኒካዊ ሂደቶች ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርቧል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ባደረገው ጥናት በ2030 አፍሪካ ለአየር ንበረት ቀውስ መታደጊያ 400 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋት በጥናቱ አመላክቷል፡፡
|ደመቀ ከበደ - ከአፍሪካ ሕብረት - አዲስ አበባ|