በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን እማካይነት በኢትዮጵያ መንግሥትና ሕወሓት መካከል የሰላም ንግግር ለማካሔድ ኦክቶበር 24 ቀን 2022 ደቡብ አፍሪካ እንዲካሔድ ቀን መቆረጡ ተገለጠ።
የሰላም ንግግሩን ለማካሔድ ቀን ቆርጦ ግብዣ ያቀረበው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን መሆኑን ያስታወቁት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የፀጥታ አማካሪ ናቸው።
የሰላም ንግግሩ ዕሳቤ አዲስ ሳይሆን ቀደም ሲልም ኦክቶበር 8 በተመሳሳይ መልኩ ደቡብ አፍሪካ እንደሚካሔድ በአፍሪካ ኅብረት በኩል ለሁለቱ ወገኖች ጥሪ ቀርቦ ያለስኬት መክኖ ቀርቷል።
በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና በሕወሓት ጦር መካከል የሚደረገው ወታደራዊ ግጭት አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል።
በዚህ ሳምንት ውስጥ ከመንግሥት በተሰጠ መግለጫ ሽሬ፣ አላማጣና ቆቦ ከተሞችን ከሕወሓት እጅ አውጥቶ በቁጥጥሩ ስር ማድረጉን ገልጧል።
አምባሳደር ሬድዋን መንግሥታቸው በሰላም ንግግሩ ላይ ተሳታፊ እንደሚሆን ቢያስታውቁም በሕወሓት በኩል እስካሁን የተሳታፊት ማረጋገጫም ሆነ የእምቢታ ቃሎች ገና አልተደመጡም።