የጤና ኢንሹራንስ ድርጅቱ ሜዲባንክ ከተጠርጣሪ ዳታ ጠላፊ ቡድን የደረሰውን መልዕክት ተከትሎ ደምበኞቹን ይቅርታ ጠይቋል።
የኢንሹራንስ ኩባንያው ከፌዴራል መንግሥቱ የሳይበር ደኅንነት ኤጂንሲዎች ጋር በመተባበር የተጠለፉበትን የደንበኞቹን ዳታ አስመልክቶ ብርቱ ምርመራ እያካሔደ መሆኑን ገልጧል።
የሳይበር ደኅንነት ሚኒስትር ክሌየር ኦኒል የአውስትራሊያ ኩባንያዎች የደምበኞችን ዳታ ጠብቆ ለመያዝ አሁን እያደረጉ ካሉት ጥረቶች የበለጠ ታካይ ጥረቶችን ማድረግ እንደሚገባቸው አሳበዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊትም የአውስትራሊያ ሁለተኛው ግዙፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ኩባንያ ኦፕተስ ደንበኞች መሰረቁ ይታወሳል።
ሰሜን ኢትዮጵያ
በሰሜን ኢትዮጵያ በኢትዮጵያና መንግሥትና ሕወሓት መካከል እየተካሔደ ያለውን ግጭት አስመልክቶ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ስላስከተላቸውና የሚያስከትላቸውን የጤና ቀውሶች አስመልክተው ስጋታቸውን ገልጠዋል።
አክለውም፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለቀውሱ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጥ አበረታተዋል። የዘር ማጥፋት እንዳይደርስም ጠባብ መስኮት ነው ሲሉ አመላክተዋል።
በሌላም በኩል የሰብዓዊ መብቶች ተመልካች (HRW) ኦክቶበር 18 ባወጣው መግለጫ በመንግሥት ቁጥጥር ስር በገባችው ሽሬ ከተማ ባሉት ሰዎች ላይ እንደ ከዚህ ቀደሙ በኢትዮጵያና ኤርትራ ጦሮች የግድያና ሰቆቃ ተግባራት እንዳይፈፀሙ ስጋት አለኝ ብሏል።
አያይዞም፤ የትግራይ ተዋጊዎችም በአማራ ክልል ቆቦ ከተማ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያ መፈፀማቸውንና የንብረት ውድመቶችን ማድረሳቸውን አመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ከሕወሓት እጅ አውጥቶ በራሱ ቁጥጥር ስር ባደረጋቸውና በሚያደጋቸው ከተሞች ሰብዓዊ እርዳታዎች ቀልጥፈውና ተሳልጠው እርዳታ ለሚሹ ወገኖች እንዲደርሱ የሚያስችል አንድ አስተባባሪ ኮሚቴ ማቋቋሙንና ሥራውንም እንደጀመረ አስታውቋል።
ኮሚቴው የተዋቀረው ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ ከአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ፌደራል ፖሊስና የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ተውጣጥቶ ነው።
የኮሚቴው ሰብሳቢ ሆነው የተመደቡት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሲሆኑ፤ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቱ የሽሬ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ እንደሚካሔድ ገልጠዋል።
ይህንኑ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትና መሠረታዊ አገልግሎቶችን የማስቀጠል ትልምና ሂደትን አስመልክቶ የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጥቅምት 8 ቀን 2015 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሰሞኑን ከመቀሌ ሰሜናዊ ምዕራብ 140 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውን ሽሬ ከተማን፣ እንዲሁም ከመቀሌ 170 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለችውን ኮረምንና በ180 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኘውን አላማጣን በቁጥጥሩ ስር እንዳደረገ አመልክቷል። .