የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ከሰብዓዊ እርዳታ እጥረት ጋር ታክሎ በዝናብ መዘግየት ሳቢያ በሚፈጠረው ብርቱ ድርቅ በዚህ ዓመት እስከ 20 ሚሊየን የአፍሪካ ቀንድ ሰዎች ሊራቡ እንደሚችል አስታወቀ።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም አያይዞም ሶማሊያ በመጪዎቹ ስድስትወራት ውስጥ ለረሃብ እንደምትጋለጥ፣ 7.2 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ከወዲሁ በቂ ምግብ እያገኙ እንዳልሆነና ኬንያም በእጅጉ ለከፋ ረሃብና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንደምትጋለጥ አመላክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ ደቡብ ኢትዮጵያ ውስጥ ሶስት ሚሊየን ያህል የቀንድ ከብቶች ለሞት መዳረጋቸውም ተገልጧል።
የተመድ ሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ኤጄንሲ በበኩሉ ምንም እንኳ ወደ አፋርና ትግራይ የረድዔት አቅርቦቶች ሁኔታ መሻሻል ቢያሳዩም በገደቦችና ግጭቶች ሳቢያ ሰሜናዊ የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ ረድዔቶችን ለማዳረስ አዋኪ መሆኑን ጠቅሷል።
ኤጀንሲው በትግራይ ምሥራቃዊ ዞን የምትገኘው ኢሮብ ወረዳ ከ33 ሺህ በላይ ሰዎች (65 ፐርሰንት ያህል የወረዳዋ ነዋሪዎች) ውስን እርዳታ ብቻ ማግኘታቸውንና ለብርቱ የምግብ ዋስትና እጦት መጋለጣቸውንም አመልክቷል።
አያይዞም፤ በአማራ ክልል የረድዔት ተደራሽነት ቢሻሻልም በሰሜን ጎንደር፣ ዋግኽምራና ሰሜን ወሎ ዞኖች ተደራሽነቱ አዋኪ ስለመሆኑ ተገልጧል።
የአካባቢውን መንግሥት አኃዝ የጠቀሰው ሪፖርት ከጃኑዋሪ 2022 አንስቶ በዋግኽምራ ዞን 61,000 እንዲሁም በሰሜናዊ ወሎ ዞን ከ57,000 በላይ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መኖራቸውን አስፍሯል።
በተጨማሪም ከ51,000 በላይ ሰዎች በውስጣዊ ውጥረቶች ሳቢያ ከኦሮሚያ ክልል ወደ አማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ተፈናቅለው መሔዳቸውን ጠቁሟል።