የ37 ዓመቷን የኒውዚላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አደርን ከኃላፊነትን በራሳቸው ፈቃድ መልቀቅን ተከትሎ፤ የ44 ዓመቱ የትምህርትና ፖሊስ ሚኒስትር ክሪስ ሂፕኪንስ በነገው ዕለት የጠቅላይ ሚኒስትር በትረ መንግሥትን ሊጨብጡ ነው።
ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ዕጩ ሆኖ ለመቅረብ ለሚሹ የኒውዝላንድ ሌበር ፓርቲ ምክር ቤት አባላት እስከ ዛሬ ጠዋት ሶስት ሰዓት በተቆረጠው ቀነ ገደብ ከክሪስ ሂፕኪንስ በስተቀር የቀረበ ዕጩ ባለመኖሩና የፓርቲያቸው ድጋፍም የተቸራቸው በመሆኑ በነገው ዕለት አዲሱ የኒውዝላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለ መሐላ ይፈፅማሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አደርንም ሙሉ በሙሉ ኃላፊነታቸውን አስረክበው ከስልጣናቸው ይሰናበታሉ።
የሂፕኪንስን ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆንን አስመልክቶ በቀዳሚነት የ"እንኳን ደስ ያለዎት" መልዕክት ያስተላልፉት የአውስትራሊያው ሌበር ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑ፤ ከሂፕኪንሰን ጋር በስልክ ተነጋግረዋል።
በመጪዎቹ ጊዜያትም አብረዋቸው ለመሥራት እንደሚሹ ያላቸውን ፍላጎት ገልጠዋል።
አልበኒዚ - ጌትስ
ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልበኒዚ ዛሬ ቅዳሜ ጃኑዋሪ 21 ኪሪቢሊ ሃውስ ከማክሮሶፍት መሥራቹ ቢል ጌትስ ጋር ተገናኝተው yeአየር ንብረት ለውጥ፣ የኃይል ምንጭና የጤና ጉዳዮችን አንስተው ተወያይተዋል።
አቶ ጌትስ አውስትራሊያን እየጎበኙ ያሉት ከጌትስ ፋውንዴሽንና በቴክኖሎጂ የአየር ብክለትን ለመቀነስ፣ ዘላቂና አስተማማኝ የኃይል ምንጭ ለማበርከት ተነሳሽነት ወስዶ ካለው ብሬክስሩ ኢነርጂ ኩባንያ ተወካዮች ጋር በመሆን ነው።
የማይክሮሶፍት መሥራቹ የወባ በሽታን ከሪጂኑ ለማጥፋት ከአውስትራሊያ ጋር በሽርካነት እየሠሩ ይገኛሉ።