በብዝሃ ሕይወት ሳይንቲስትነት አንቱታን ያተረፉት ሎሬት ዶ/ር ተወልደብርሃን ገብረእግዚአብሔር ባደረባቸው ሕመም በ83 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪ እና ተከራካሪ የነበሩት ዶ/ር ተወልደብርሃን ገብረእግዚአብሔር ከአባታቸው ከቄስ ገብረእግዚአብሔር ዮሐንስ እና ከእናታቸው ወ/ሮ መዓዛ ወልደ መድኅን በትግራይ ክልል ዐድዋ ርባገረድ አካባቢ የካቲት 12 ቀን 1932 ዓ.ም ተወለዱ።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በንግሥተ ሳባ 1ኛ ደረጃ እንዲሁም ወደ ጀኔራል ዊንጌት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በማምራት በ1959 ዓ.ም በከፍተኛ ውጤት ወደ ቀድሞው ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተዋል።
ሎሬት ዶ/ር ተወልደብርሃን በሕይወት ዘመናቸው ለአገራቸው ያበረከቱት አስተዋጽኦ እና አርዓያነታቸው በጉልህ ቀለም ከሚጻፍላቸው ጀግና ኢትዮጵያዊያን መካከል በግንባር ቀደምትነት የተቀመጡ ነበሩ።
በብዝሃ ሕይወት ጥናት እና ምርምርም በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ያገኙ ታላቅ ምሁር ነበሩ፡፡
ዶ/ር ተወልደ ብርሃን የሦስት ሴቶች ልጆች አባት የነበሩና ብዙዎችን በማሳደግም ለወግ ማዕረግ ያበቁ መሆናቸውን የቅርብ ወዳጆቻቸው ለኤስቢኤስ ገልጸዋል፡፡
በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ አገልግሎት የተከበረ ሥም ያላቸው ዶክተር ተወልደ በዘርፉ ላደረጉት ምርምርና በጉዳዩ ዙሪያ ከፍተኛ ግንዛቤ እንዲፈጠር ላደረጉት ጥረት በፈረንጆቹ 2000 Right Livlihood Award ሽልማት አግኝተዋል፡፡ በተጨማሪም በፈረንጆቹ 2006 ዓመት የተባበሩት መንግሥታት በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሰዎች የሚሰጠውን Champions of the Earth ሽልማት አግኝተዋል፡፡ የተማሩበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በ1997 የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷቸዋል፡፡
ዶ/ር ተወልደ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ፋኩልቲ ዲን ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ ከ1975 እስከ 1983 በነበረው ዘመን ደግሞ የአስመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ ከደርግ መንግሥት መውደቅ በኋላ ለብዙ ዓመታት በሚታወቁበት የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተርነት አገልግለዋል፡፡
ዶክተር ተወልደ ገብረእግዚአብሔር የደራሲ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ወንድም መሆናቸው ይታወቃል፡፡
(ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ)