የኬንያ ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ መድረክ ላይ ተገኝተው የተመድ ፀጥታ ምክር ቤትን ረብ የለሽና ኢ-ዲሞክራሲያዊ ሲሉ ተናገሩ።
አቶ ሩቶ በንግግራቸው ወቅት የሄይቲን ጉዳይ ነቅሰው በማንሳት፤ የተባበሩት መንግሥታት ሄይቲን ገጥመዋት ላሉት ተግዳሮቶች ትድግና አስቸኳይ ፍኖተ ካርታ ዘርግቶ ሕብረ ብሔራዊ ፀጥታ አስከባሪ ኃይል ድጋፍ እንዲልክም አሳስበዋል።
የኬንያው ፕሬዚደንት የዓለም አቀፍ ፋይናንስ ተቋማትን አስመልክተው የተናገሩ ሲሆን፤ አክለውም፤
"የተባበሩት መንግሥታት ፀጥታው ምክር ቤት ረብ የለሽ፣ ኢ-ዲሞክራሲያዊ፣ አካታች ያልሆነ፣ ሁሉን አቀፍ ውክልና የለሽ ስለመሆኑ ማረጋገጫ የሚሻ ካለ፤ በእዚያ ሳቢያ በዓለማችን ላይ በአሁኑ ወቅት ተንሰራፍቶ ያለው የተወሰኑ ተዋንያን ተጠያቂነት ሳያገኛቸው የሉላዊ ጉዳዮች መከወን ነው" ብለዋል።
ካናዳና ሕንድ
የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ካናዳ ውስጥ በተፈፀመው የሲክ ተገንጣይ ቡድን መሪ ሃርዲፕ ሲንግ ኒጃር ግድያ የሕንድ እጅ እንዳለበት ፍንጮች መኖራቸውን ዳግም አንስተው ተናግረዋል።
ኒጃር ሕንድ ውስጥ "አሸባሪ" ካናዳ ውስጥ በ"ሃይማኖት መሪነት" ይታወቃሉ።
ሕንድ በአሸባሪነት ከመፈረጅም አልፋ ለእስር ለመዳረግ አቶ ኒጃር የት እንደሚገኙ ለጠቆመ 1 ሚሊየን ሩፒ ወይም 9,710 ፓውንድ ወሮታ ለመክፈል ማስታወቂያ አውጥታለች።
የአቶ ኒጃር ሕይወት ካናዳ ውስጥ ያለፈው ጁን 18 ሁለት ጭምብል ባጠለቁ ግለስቦች እጅ ነው።
አቶ ትሩዶ የሕንድን በሕንዳዊው ካናዳዊ ዜጋ ግድያ እጇ የለባት ስለመሆኑ መንግሥታቸውን ያለውን መረጃ እስካሁን ያላቀረቡ ቢሆንም፤ የሕንድ መንግሥት ግድያውን አስመልክቶ እውነት ላይ የተመሰረተ ዕልባት ለማበጀት ከካናዳ ጋር ሊነጋገር እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሕንድ በሁለቱ አገራት መካክለ ያለው ልዩነት እየሰፋ መሔድን ተከትላ ለካናዳ ዜጎች ቪዛ መስጠትን ገትታለች፤ እንዲሁም ወደ ካናዳ ለሚሔዱ ዜጎቿ በተለይም ተማሪዎች ደህንነታቸውን ነቅተው እንዲጠብቁ የጉዞ ማስጠንቀቂያ አውጥታለች።