የቻይና ከፍተኛ ዲፕሎማት ዋንግ ዪ የደህንነት ጉዳይን አስመልክተው ከሩስያ ጋር ለመነጋገር እንደሚሹ ለሩስያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ገልጠዋል።
አቶ ዋንግ ከሩስያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል።
የዲፕሎማቱ የሩስያ ጉብኝት የተካሔደው የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ቻይና ለሩስያ የዩክሬይን ወረራ የቁሳቁስ ድጋፍ እንዳታደርግ ማሳሰቢያ መስጠትን ተከትሎ ነው።
ይሁንና አቶ ዋንግ የቻይና-ሩስያ ግንኙነት "እጅግ ጠንካራና እየተለወጠ በመሔድ ባለው ዓለም አቀፍ ሁኔታ ማናቸውንም ፈተና የሚቋቋም ነው" ብለዋል።
በሌላ በኩል የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ሩስያ ዩክሬይንን የወረረችበትን አንደኛ ዓመት በማንሳት ተከስቶ ያለውን ሉላዊ ውጥረት በማመላከት ለኔቶ "የግንባር መስመር" ምሥራቃዊ አባል አገራት የደህንነት ማረጋገጫ ቃል ሰጥተዋል።
የቻይናው ፕሬዚደንት ሺ ሞስኮ ዘልቀው ከሩስያው አቻቸው ጋር የሚገናኙ ሲሆን፤ ዓርብ ዕለት "የሰላም ንግግር" ያደርጋሉ።
ሆኖም፤ የዩክሬይን ፕሬዚደንት ቭላድሚር ዜሌንስኪ የሩስያ ወታደሮች የዩክሬይን ምድርን ለቅቀው እስካልወጡ ድረስ ከሩስያ ጋር የሰላም ንግግር ለማድረግ እንደማይፈቅዱ አስታውቀዋል።