ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ ለድምፅ ለፓርላማ ሕዝበ ውሳኔ የሚውለውን ጥያቄ ዛሬ ይፋ አደረጉ።
ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል የአውስትራሊያ ነባር ዜጎች በፓርላማ ተደማጭ ድምፅ እንዲኖራቸው ለሕዝበ ውሳኔው የሚቀርበው መጠይቅ 'የታቀደ ሕግ፤ ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል ለአውስትራሊያ ነባር ዜጎች ዕውቅና በመቸር የአቦርጂናልና ቶረስ መሽመጥ ድምፅ ለመመሥረት። ለዚህ የማሻሻያ እቅድ ይሁንታዎን ይቸራሉ?' የሚል ነው።
ይሁንና የተቃዋሚ ቡድን መሪ ፒተር ዳተን የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሕዝበ ውሳኔ ጥያቄ ይፋ ማድረግ ተከትሎ፤ ለድምፅ ለፓርላማ ፓርቲያቸው ድጋፉን ስለመስጠት አለመስጠት ያለውን አቋም ከመግለፅ ተቆጥበው በምትኩ መንግሥት ድምፅ ለፓርላማ እንደምን ግብር ላይ እንደሚውልና ሕገ መንግሥታዊ ለውጡ ሊያስከትላቸው ስለሚችለው ሕጋዊ ተፅዕኖዎች ዝርዝር ማብራሪያዎችን አልሰጠም በማለቱ ላይ አተኩረዋል።
አቶ ዳተን ፓርቲያቸው ድምፅ ለፓርላማን አስመልክቶ ያለውን አቋም በተመለከተ ስብሰባውን ሲያካሂድ የሚወስንበት ጉዳይ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ የናሽናልስ ፓርቲ መሪ ዴቪድ ሊትልፕራውድ ፓርቲያቸው የድምፅ ለፓርላማ ምሥረታን በመቃወም አቋሙ ፀንቶ ያለ መሆኑን ገልጠዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ሕዋ ኤጄንሲ አስተዳዳሪ፤ ኤጄንሲው ጨረቃ ላይ ውኃ መኖር አለመኖሩን ለማጣራት ጠፈርተኞችን ወደ ደቡብ ዋልታ ለመላክ ዕቅድ መያዙን ገለጡ።
የቀድሞ ሴናተርና ጠፈርተኛ ቢል ኔልሰን ዕቅዱን የገለጡት በዛሬው ዕለት በአውስትራሊያ ብሔራዊ ፕሬስ ክለብ ተገኝተው ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነው።
አቶ ኔልሰን፤ በአንድ ሳምንት ውስጥ ብሔራዊ የጠፈር ጉዞና ሕዋ አስተዳደር ተጓዥ ጠፈርተኞቹ እነማን እንደሚሆኑ ይፋ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል።