ለዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ ዝክረ መታሰቢያ ይፋ የሐዘን መግለጫ ለማውጣትና የንጉሥ ቻርልስ ሳልሳዊን የዙፋን ውርስ ዕውቅና ለመቸር ዛሬ የተሰየመው የአውስትራሊያ ፓርላማ ሪፐብሊክ የማቆም ክርክርንም አስተናግዷል።
የአውስትራሊያ ግሪንስ ፓርቲ መሪ አዳም ባንድት አውስትራሊያውያን ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት ንግሥት ኤልሳቤጥ ከበሬታ የተመላው ሐዘናቸውን በመግለጥ ወደ ሪፐብሊክ ማምራት እንደሚሹ አመላክተዋል።
ወቅቱም አውስትራሊያውያን በሳልነታቸውን የሚያሳዩበትና ወደ ፊት የመራመጃቸው ጊዜ መሆኑን በማንሳት "የእዚህች አገር ርዕሰ ብሔር በሕዝብ፣ ለሕዝብና ከሕዝብ ሊመረጥ ይገባል" ብለዋል።

በሌላም በኩል፤ የሐዘን ማፅናኛ ቃል ለንጉሣዊው ቤተሰብ ያቀረቡት የግሪንስ ሴናተር ሳራ ሃንሰን-ያንግ ወቅቱ አውስትራሊያዊ ርዕሰ ብሔር ለመሰየም ወደ ፊት የመራመጃ ጊዜ እንደሆነ አመላክተዋል።

አያይዘውም "ንጉሥ ቻርልስ ሳልሳዊ የእኛ ምርጫ አይደሉም። ምርጫው የአውስትራሊያውያን መሆን ሲገባው ያ አልሆነም"
"የእኛ ርዕሰ ብሔር መሆን ያለበት የእኛ የሆነ አውስትራሊያዊ ነው" ሲሉ ለሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ አሰምተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ የአውስትራሊያ ሪፐብሊክ ንቅናቄ የንግሥቲቱን የቀብር ሥነ ሥርዓትና ብሔራዊ የሐዘን ቀን ፍፃሜን ተከትሎ ከዘውዳዊ ሥርዓት ለመላቀቅ ጊዜ መጥፋት እንደሌለበት የንቅናቄው ሊቀመንበር ፒተር ፊትዝመንስ አሳስበዋል።
አክለውም "በውልደት መብት መግዛት፤ በአውስትራሊያ ዲሞክራሲ ውስጥ ሥፍራ የለውም" ብለዋል።
"ዕሳቤው እንደ ዘውዳዊ ሥርዓቱ ሁሉ ለአውስትራሊያውያን ዕሴቶች ባዕድ ነው። ማንም ሰው ለውጭ ንጉሥ ወይም ርዕሰ ብሔር የታማኝነት ቃል ኪዳን ሊፈጽም አይገባም" ብለዋል።
የአውስትራሊያ ነባር ዜጎች የምክር ቤት አባላትም በበኩላቸው የንግሥቲቱ ሕልፈተ ሕይወትና የቅኝ ግዛት አሻራ አሳድሮባቸው ያለውን ስሜት በተዛነቀ መንፈስ ገልጠዋል።
የሪፐብሊክ ምሥረታ ደጋፊና ዓላማውንም አራማጅ የሆኑ የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ የንግሥቲቱን ሞት ተከትሎ ፈጥነው የሪፐብሊክ ክርክርን ማንሳት እንደማይሹ በተደጋጋሚ ገልጠዋል።

