ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ነሐሴ 22 የተጀመረው የብሪክስ ጉባኤ ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ 18 የአባላቱን ቁጥር ለማስፋት ተስማምቶ ስድስት አገራትን በሙሉ አባልነት መቀበሉን አስታወቀ።
በሙሉ አባልነት የታከሉት አገራት ከአፍሪካ ኢትዮጵያና ግብፅ፣ ከደቡብ አሜሪካ አርጀንቲና፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ መሆናቸውን የጉባኤው ሰብሳቢ ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ በይፋ አስታውቀዋል።
በአዲስ አባልነት ብሪክስን የተቀላቀሉትን አገራት የዋነኛ መሥራች አገራት መሪዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልካም ምኞት መግለጫ ንግግር አድርገዋል።
የ15ኛው ብሪክስ ጉባኤ አስተናጋጅዋ አገር ደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ የስድስቱ አገራት በሙሉ አባልነት መታከል የመጀመሪያው ምዕራፍ እንደሆነና በቀጣዩ ምዕራፍም ተጨማሪ አገራት እንደሚታከሉ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮም የኢትዮጵያን የብሪክስ ሙሉ አባልነት መብቃት አስመልክቶ ለመላው ኢትዮጵያውያን የ "እንኳን ደስ አላችሁ" መልዕክት አስተላልፏል።
አዲሶቹ የብሪክስ አባል አገራት ሙሉ የአባልነት ሥፍራቸውን ከጃኑዋሪ 1፣ 2024 ጀምሮ ይይዛሉ።
ቀጣዩ የብሪክስ ጉባኤ የሚካሔደው ሩስያ ውስጥ ሲሆን፤ ብሪክስ (BRICS) የሚለው ስያሜ የእንግሊዝኛ ምሕፃረ ቃል የ (Brazil, Russia, India, China እና South Africa) መገለጫ በመሆኑ ከአዲሶቹ ስድስት አገራት መታከል ጋር ተያይዞ የመጠሪያ ስያሜውን ይለውጥ እንደሁ ለጊዜው አልተገለጠም።