ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ በፌዴራል ምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ፓርቲያቸው ቃል የገባውን የሮቦዕዳ ምርመራ ዕውን ለማድረግ የሮያል ኮሚሽን መሰየማቸውን አስታወቁ።
የሮቦዕዳ ባለፈው የሞሪሰን መንግሥት ወቅት በሺህዎች የሚቆጠሩ ድጎማ ተቀባዮች የሌለባቸውን የሴንተርሊንክ ዕዳ ባለዕዳ አድርጎ ያቀረበ ድርጊቱም በፍርድ ቤት ሕጋዊ አለመሆኑ በ2019 ተገልጧል።
በብይኑ መሠረትም የፌዴራል መንግሥቱ $1.9 ቢሊየን ዶላርስ የካሣ ክፍያ እንዲፈፅም ተደርጓል።
አዲስ የተሰየመው ኮሚሽን ፕሮግራሙን ማቋቋም ለምን እንዳስፈለገ፣ ተጠያቂው ማን እንደሚሆን፣ አስፈላጊ የተባለበት ምክንያት ምን እንደሆነና መንግሥትን ያስወጣው ወጪ ዝርዝርን የሚመረምር ይሆናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ በንግግራቸው ወቅት "400 ሺህ ያህል አውስትራሊያውያን የዚህ ጨካኝ አሠራር ሰለባዎች መሆናቸውን እናውቃለን" ያሉ ሲሆን፤ አክለውም ኮሚሽኑ እንዲያ ያለ አሳፋሪ ተግባር ዳግም እንዳይፈፀም የሚሆንበትን ብልሃት እንዲያመልክትም ተጨማሪ ተግባር የተሰጠው መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህንኑ ተግባር ግብር ላይ ለማዋልም የፌዴራል መንግሥቱ የቀድሞዋን የኩዊንስላንድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዋና ዳኛ ካትሪን ሆልምስን ሮያል ኮሚሽነር አድርጎ ሰይሟል።
***
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ ኢትዮጵያ ውስጥ ዳግም ግጭት በመቀስቀሱ ዜና "ጥልቅ ኃዘንና ድንጋጤ" የተሰማቸውን መሆኑን ገለጡ።
ዋና ፀሐፊው በመንግሥትና በሕወሓት መካከል በግጭት ፈንታ ወደ አስቸኳይ ተኩስ አቁምና የሰላም ንግግር እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።
ትናንት በኢትዮጵያ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በኩል በወጣው መግለጫ ሕወሓት ከለሊቱ 11 ሰዓት ላይ በምሥራቅ ግንባር በቢሶ በር፣ ዞብልና ተኩለሽ አቅጣጫዎች ጥቃት መክፈቱን አመልክቷል።
በሌላም በኩል ሕወሓት ወታደራዊ ዕዝ ባወጣው መግለጫ፤ ኦገስት 24 የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሠራዊት 6ኛና 8ኛ እግረኛ ጦርና የ2ኛ፣ 6ኛ እና 8ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦሮች በጮቤ በር፣ ጃኖራ፣ ጉባጋላ፣ ያለው፣ አላማጣ፣ ባላ እና ቢሶ በር አቅጣጫ ጥቃቶችን መሰነዘሩን ገልጧል።
ይህ በንዲህ እንዳለም፤ የተመድ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር ዲቪ ቢዝሊ የሕወሓት ባለስልጣናት መቀሌ ከሚገኘው የዓለም ምግብ ፕሮግራም 500 ሺህ ሊትር ነዳጅ አሰርቀዋል ሲሉ በቲዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።
ድርጊቱንም በአሳፋሪነት ገልጠው፤ የተወሰደው ነዳጅ በአስቸኳይ እንዲመለስ ጠይቀዋል።