ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ የገናን በዓል አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር "ከቤተሰብና ከወዳጆች ጋር በጋራ ዘና መባያ" እና ለበርካታ አውስትራሊያውን "የዕምነት ማዕከል" መሆኑንም አመላክተዋል።
አክለውም፤ በዛሬዋ ዕለት በሥራ ገበታ፣ በበጎ ፈቃደኝነት፣ የድንገተኛ አደጋ ደራሽና በመከላከያ ግዳጅ ላይ ተሠማርተው ያሉ አውስትራሊያውያንን አስተዋፅዖዎች በማንሳት "ለአገልግሎቶቻቸሁ ምሥጋናዬንና አድንቆቴን አቀባለሁ" ብለዋል።
የፌዴራል ተቃዋሚ ቡድን መሪ ፒተር ዳተን በበኩላቸው 2022 በተፈጥሮ አደጋ ክስተት፣ በመጠነ ሰፊ ዳታ ስርቆትና በዳግማዊት ኤልሳቤጥ ሕልፈተ ሕይወት "እጅግ አዋኪ ዜና" አስቸጋሪ ዓመት እንደነበር አውስተዋል።
አያይዘውም፤ የኑሮ ውድነት አውስራሊያውያንን እየጎዳ መሔድ ላይ መሆኑን በመጥቀስ፤ በመጪዎቹ ወራትና ዓመታት የማኅበረሰባትንና መንግሥትን ድጋፎች ግድ እንደሚልም አመላክተዋል።
በዓለ ገናውንም አስመልክተው፤ ዘመድ አዝማድ አልባ አውስራሊያውያን በዓለ ገናን በብቸኝነት እንዳያከብሩ በክርስቲያን መንፈስ እንዲጎበኟቸውም አሳስበዋል።
እንዲሁም "ምንም እንኳ ዓመቱ አዋኪ የነበረም ቢሆን፤ በዓለ ገና ለአውስትራሊያውያን ምን ያህል ዕድለኞች እንደሆንንን፣ በዓለም ምርጥ በሆነች አገር የምንኖር መሆኑንም ዳግም የምንገልጥበት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።