በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደርና ልዩ መልዕክተኛ ሃደራ አበራ አድማሱ ለአውስትራሊያ የንግድና ውጭ ጉዳይ ዲፓርትመንት የፕሮቶኮል ሹም ኢያን ማክኮንቪል ቅጂ የሹመት ደብዳቤያቸውን ሰኔ 19 ቀን 2015 ማቅረባቸውን በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ።
አምባሳደር ሃደራ የሹመት ደብዳቤያቸውን ባቀረቡበት ወቅትም "በኢትዮጵያና አውስትራሊያ መካከል ላለፉት 60 ዓመታት የዘለቀውን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር የኢትዮጵያ መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን፤ በማዕድንና ኢነርጂ፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉድኝት፣ በንግድ፣ በሙዋዕለ ንዋይ ፍሰት፣ በቱሪዝምና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፎች የሁለትዮሽ ግንኙነቶቹን ለማስፋት እንደሚሠሩ" መግለጣቸውን ኤምባሲው አመላክቷል።
አያይዞም "በሁለቱ አገራት መካከል እንደ ድልድይ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙትን በአውስትራሊያ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ተሣትፎ የበለጠ በማጠናከር ዳያስፖራው በአገሩ ጉዳይና በሁለትዮሽ ግንኙነቱ የሚኖረው ሚና የጎላ እንዲሆን እንደሚሠሩ" መናገራቸውን አስታውቋል።
በአውስትራሊያ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፕሮቶኮል ሹም ማክኮንቪል "ኢትዮጵያ በአፍሪካ አኅጉር ያላት ሚና የላቀ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አውስትራሊያ ትኩረት ከምትሰጣቸው አገራት መካከል አንዷ መሆኗንና የኢትዮጵያ መንግሥት ኤምባሲውን በሙሉ አቅሙ ሥራ ማስጀመሩ የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን ለማጠናከር ትልቅ ሚን የሚኖረው መሆኑን" እንደገለጡም ተመልክቷል።