ብርቱ ፉክክር በታየበት የስድስተኛው ቀን የፊፋ ዓለም ዋንጫ 2022 ውድድር አዘጋጇ አገር ኳታር በሴኔጋል ቡድን 3 ለ 1 በመረታት ከውድድሩ ላትመለስ በመሰናበት የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች።
ቦዩሌይ ዲያ፣ ፋማራ ዳይዲዮና ባምባ ዲንግ ለሴኔጋል በተከታታይ ሶስት ግቦችን ሲያስቆጥሩ መሐመድ ሙንታሪ ለኳታር አንድ ግብ በማስቆጠር የአዘጋጇን አገር ደጋፊዎች ላፍታም ቢሆን አስፈንድቋል።

ብርቱ በሆነ ፍልሚያና አስገራሚ በሆነ አጨራረስ ኢራን ዌልስን 2 ለ 0 አሸንፋለች።
ለኢራን ሁለቱን ግቦች ያስቆጠሩት ሩዝቤህ ቼሽሚ እና ራሚን ሪዜይን ናቸው። ሁለቱም ግቦች በዌልስ መረብ ላይ ያረፉት ሙሉው የ90 ደቂቃው ጨዋታ ተጠናቅቆ ተጨማሪ በሆነው 9 ደቂቃ ጨዋታ ወቅት ሲሆን፤ ቼሽሚ የመጀመሪያዋን ግብ በታካዩ ስምንተኛ ደቂቃ ላይ ሪዜይን ሁለተኛዋን ለፍፃሜ ጥቂት ሰከንዶች ጉዳይ ላይ ነበር በግብነት ያስቆጠሩት።
የኢራን ቡድን ዌልስን 2 ለ 0 ማሸነፍ ከአሜሪካ ጋር ለሚገጥመው ግጥሚያ ከፍተኛ በራስ የመተማመን መንፈስን ይፈጥርለታል የሚል ግምት አሳድሯል።

የእንግሊዝና ዩናይትድ ስቴትስ የመጀመሪያው አጋማሽ ግጥሚያ አንዱ ቡድን በሌላው ላይ ተደጋጋሚ ማጥቃቶችን ያሳየበት ውድድር ነበር።
ለዩናይትድ ስቴትስ ምንም እንኳ የክርስቲያን ፑሊቺች ጥረቶቹ ለመረብ ባይበቁም የግቡን ብረት የታከከችና ተጨማሪም ለግብነት የተጠጋ ሙከራን በማድረግ በእንግሊዝ ላይ ስጋትን ለምሳደር በቅቷል።
የዩናይትድ ስቴትስ ቡድን ከዕረፍት በኋላም በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታ በርካታ የማዕዘን ምቶችን በማግኘት የእንግሊዝን ቡድን አስጨንቋል።
ይሁንና የእንግሊዝ ቡድን በፊናው ወደ ጨዋታው መገባደጃ ግድም በማርከስ ራሽፎርድ እና ሃሪ ኬን አማካይነት ለግብነት የተቃረቡ ጥረቶችን አድርጓል።
ሆኖም ሁለቱም ቡድኖች ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው 0 ለ 0 በሆነ ውጤት ተለያይተዋል።
በቀጣዩ የ16 ቡድኖች ውድድር ተጋጣሚነት ለመብቃት ፈታኝ ፍልሚያ ይጠብቃቸዋል።