የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ኦክቶበር 25 ቀን 2022 / ጥቅምት 15 ቀን 2015 በሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ስም ባወጡት መግለጫ አገራቸው በአፍሪካ ኅብረት መሪነት በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተጀመረውን የሰላም ንግግር በመልካም ጎኑ እንደምታየው አመላክተዋል።
አያይዘውም፤ የልዑካን ቡድናቱ በንግግራቸው ወቅት ለግጭቱ ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ብርቱ ትኩረት እንዲሰጡና የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ በአስቸኳይ የመድረስ አስፈላጊነት ቀዳሚ ጉዳይ መሆኑን አስመልክቶ መንግሥታቸው የሚያበረታታ መሆኑን ገልጠዋል።
እንዲሁም፤ ልዑካኖቹ ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያሻቸው ሁሉ አንዳች ገደብ ያልተጣለበት ተደራሽነት እንዲኖር፣ የሰላማዊ ሰዎችን ደኅንነት የሚያስጠብቁ መሥፈርቶች ግብር ላይ እንዲውሉና የኤርትራ ጦር ከሰሜን ኢትዮጵያ ለቅቆ እንዲወጣ ጥሪ የሚያቀርቡ መሆኑን አስታውቀዋል።
አቶ ብሊንከን ደቡብ አፍሪካን ስለ አስተናጋጅ አገርነቷና ለአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ተወካይ ኦባሳንጆ፣ የቀድሞዋ ደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዚደንት ምላምቦ-ንጉካ እና የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚደንት ኬንያታ ለሽምገላ ተግባራቸው መቃናት ስለቸረችው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አክለውም፤ ከኬንያው ፕሬዚደንት ሩቶ፣ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና የደቡብ አፍሪካዋ የዓለም አቀፍ ግንኙነቶችና ትብብር ሚኒስትር ፓንዶር ጋር ግጭቱ ፈጥኖ እንዲከላ የተነጋገሩ መሆኑን አመልክተዋል።

Kenyan President William Ruto (L), Ethiopia's Prime Minister Abiy Ahmed (C), and Minister of International Relations and Cooperation Naledi Pandor (R). Credit: Billy Mutai/Anadolu Agency via Getty Images / Mohammed Abdu Abdulbaqi/Anadolu Agency/Getty Images / Sydney Seshibedi/Gallo Images via Getty Images