በሱዳን መከላከያ ሠራዊትና በፈጣን ድጋፍ ኃይል ጦር መካከል በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ እስካሁን ሕይወታቸው ካለፈው በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በተጨማሪ አያሌዎች ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም አሳሰቡ።
ተዛማች በሽታዎች፣ የውኃና ምግብ እጥረት፣ የጤና አገልግሎትና ክትባት መቋረጥ ለተጨማሪ ሞት አስባብ እንደሚሆኑ ተገልጧል።
በሁለቱ የሱዳን ጦሮች መከል ግጭት ከመቀስቀሱ በፊት የተባበሩት መንግሥታት 16 ሚሊየን ሱዳናውያን እርዳታ እንደሚሹ ጠቁሞ የነበረ ሲሆን፤ ግጭቱን ተከትሎ የእርዳታ ፈላጊ ሱዳናውያን ይበልጡን እንደሚያሻቅብ ተጠቅሷል።
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳመላከቱት፤ ፓራሚዲክስ፣ ነርሶችና ሐኪሞች የቆሰሉ ሰላማዊ ሰዎችን ቀርበው ለማከም እንዲሁም የሕክምና አገልግሎት መስጫዎች ዘንድም መድረስ እንዳልቻሉ ጠቁመዋል።
አያይዘውም፤ ካርቱም ውስጥ ካሉት የጤና አገልግሎት ተቋማት ውስጥ 61 ፐርሰንቱ የተዘጉ ሲሆን፤ አዘቦታዊ የሕክምን አገልግሎቶቻቸውን መስጠት ላይ የሚገኙት 16 ፐርሰንት ብቻ መሆናቸውንም ገልጠዋል።
ከግጭቱ የሸሹ ሱዳናውያን ወደ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ቻድ፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን መዝለቃቸውን የተባብሩት መንግሥታት ምክትል ቃል አቀባይ ፋርሃን ሃቅ ተናግረዋል።
የተመድ ስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እንደገለጠው ወደ ቻድ ብቻ 270,000 ሱዳናውያን አገራቸውን ጥለው ለስደት መዳረጋቸውን ጠቅሷል።