የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከነገ ታህሳስ 19 አንስቶ በጦርነት ሳቢያ ተቋርጦ የነበረውን የመቀሌ በረራውን እንደሚጀምር የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው አስታወቁ።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው ለአየር መንገዱ የበረራ ጅመራ አስባቡ በፌዴራል መንግሥቱና ሕወሓት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት መርሃ ግብር ተከትሎ አመቺ ሁኔታ መፈጠሩ እንደሆነም አስረድተዋል።
በነገው ዕለት የሚያካሒደው በቀን የአንድ ጊዜ በረራ ሲሆን፤ የተጠቃሚዎች ቁጥር መጠን ከፍ ሲልም የበረራ አገልግሎቱ ሊጨምር እንደሚችል ተገልጧል።
የቲኬት ሽያጭም ዛሬ ታሕሳስ 18 ቀን 2015 ጀምሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ወ/ሮ ፍሬሕይወት ታምሩ በበኩላቸው፤ በትግራይ 27 ከተሞች የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቶች ዳግም ለተጠቃሚዎች እየተዳረሱ መሆኑን ተናግረዋል።
በጦርነቱ ሳቢያ ውድመት የደረሰባቸው የመሠረተ ልማት አውታሮች ጥገና እየተካሔደላቸው ይገኛል።
በሂደቱም 1,800 ኪሎ ሜትር የማያንስ የፋይበር ኦፕቲክ መስመር የጥገና ሥራዎች በመከናወን ላይ እንዳሉና እስካሁን የ931 ኪሎሜትር ጥገና ሥራዎች መጠናቀቃቸው ተመልክቷል።
በሌላም በኩል፤ የኤሌክትሪክና ባንክ አገልግሎቶችም ሥራ መጀመራቸውና ከሰሞኑም መጠነ ሰፊ አገልግሎት መስጠት እንደሚቀጥሉ ተነግሯል።