የተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች የአውስትራሊያ ነባር ዜጎች የፌዴራል ፓርላማ ውስጥ ድምፅ እንዲኖራቸው ድጋፋቸውን የሚለግሱ መሆኑን በጋራ ገለጡ።
የአቦርጂናልና ቶረስ መሽመጥ ደሴተኞች የፓርላማ ድምፅ እንዲኖራቸው የጠየቀው የኡሉሩ መግለጫ ይፋ ከሆነ ዛሬ አምስተኛ ዓመቱን አስቆጥሯል።
እንዲሁም የአውስትራሊያ ነባር ዜጎች በ1967 የመምረጥ መብት ካገኙ 55 ዓመት ሞልቶታል።
አዲሱ የሌበር መንግሥት የኡሉሩ መግለጫን ግብር ላይ ማዋል ከተቀዳሚ ዋነኛ ተግባራቶቹ መካከል አንዱ መሆኑን ደጋግሞ አስታውቋል።
ይሁንና በምርጫ ድል ተነስቶ ከመንግሥትነት ወደ ተቃዋሚ ቡድንነት የዞረው የሊባራል/ናሽናልስ ጥምር ቡድን ድጋፉን ይስጥ አይስጥ አልታወቀም።
ሆኖም የአንገሊካን፣ እስልምና፣ ይሁዲ፣ ሂንዱ፣ ሲክና የተባበረው ቤተክርስቲያን እምነት መሪዎች የኡሉሩን መጠይቆች እንደሚደግፉ በአንድነት የጋራ ድምፃቸውን አሰምተዋል።
በሃይማኖት መሪዎቹ የጋራ ስብሰባ ላይ በክብር እንግዳ ሆነው የቀረቡት የነባር ዜጎች ፊልም ቀራጭዋ ራቼል ፐርኪንስ የአማኝ አውስትራሊያውያን ማኅበረሰብ አባላት የሃይማኖት መሪዎቻቸውን ፈለግ በመከተል ልባቸውን ክፍት አድርገው ብሔራዊ አንድነትን ዕውን እንዲሆን ድጋፋቸውን እንዲቸሩ ጠይቀዋል።
ፈረንሳይ - አውስትራሊያ
የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን በሌበር የሚመራ አዲስ የአውስትራሊያ መንግሥት መቆምን ተከትሎ አገራቸው ከአውስትራሊያ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነቷን መገንባት እንደምትሻ ትናንት ሐሙስ ባወጡት መግለጫ አስታወቁ።
የፈረንሳይ ፕሬዚደንታዊ ቤተ መንግሥት በሐሙሱ መግለጫው አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚን 'እንኳን ደስ ያለዎት' ብሏል።
ባለፈው ወርኃ ኦክቶበር የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን አውስትራሊያ ከፈረንሳይ ጋር ባሕር ሰርጓጅ መርከብ ለመገንባት ተዋውላ የነበረውን የ90 ቢሊየን ዶላርስ ፕሮጄክት ያለ ቅድመ ማሳሰቢያ ከሰረዙበት አንስቶ በሁለቱ አገራት መካከል የነበረው ግንኙነት ተከስቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሻክሮ ነበር።

French President Emmanuel Macron. Source: Getty
ይህንን አዲሱን አጀንዳ ግብር ላይ ለማዋልም ፍኖተ ካርታ እንደሚነደፍ ገልጠዋል።