የተቃዋሚ ቡድን መሪ አንቶኒ አልባኒዚ ከኮቪድ-19 አገግመው ዛሬ ወደ ምርጫ ዘመቻ ተመለሱ።
አቶ አልባኒዚ ባለፈው ሳምንት በኮቪድ-19 ከተጠቁ በኋላ ለሰባት ቀናት በሲድኒ መኖሪያ ቤታቸው ወሸባ ገብተው ነበር።
በዛሬው ዕለትም የሌበር ፓርቲ አገር አቀፍ የምርጫ ዘመቻ እሑድ ሜይ 1 በይፋ ወደሚከፈትባት የምዕራብ አውስትራሊያ መዲና ፐርዝ ከተማ አምርተዋል።
የሌበር መሪ ቀደም ሲል ሥራ ላይ ያውሏቸው ከነበሩባቸው ሰዓታት ውስጥ ከ16 እስከ 20 ሰዓታት እንዲቀንሱ በሐኪሞቻቸው ምክር የተቸራችው መሆኑን ጠቅሰው፤ ከሕዝብ ጋር ተገናኝተው የምርጫ ዘመቻቸውን ለማካሔድ ስንዱ መሆናቸውን ገልጠዋል።
የሌበር ፓርቲ መሪ ከወሸባ ሲወጡ የሌበር ምክትል መሪ ሪችድ ማርለስ በኮቪድ-19 ተይዘው ለሰባት ቀናት ወሸባ ገብተዋል።
በሌላም በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ዛሬ ታዝማኒያ ውስጥ የምርጫ ዘመቻ እያካሔዱ ሲሆን፤ በዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት የተነሳ የመንግሥታቸውን የምጣኔ አስተዳደር ብቃት ሬኮርድ ለመከላከል ግድ ተሰኝተዋል።
አቶ ሞሪሰን ዓለም አቀፍ ሁነቶች፣ ኮቪድ-19 እና የዩክሬይን ጦርነትን ለዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት መባባስ በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

Prime Minister of Australia Scott Morrison. Source: Getty
ዩናይትድ ስቴትስ ዩክሬይን
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ለዩክሬይን ጦር መሳሪያዎች፣ ጥይቶችና ሌሎች ወታደራዊ ቁሳቁሶች መርጃ የሚሆን 46 ቢሊየን የአውስትራሊያ ዶላርስ [[33 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላርስ]] ኮንግረስ እንዲያፀድቅላቸው ጠየቁ።
ገንዘቡ በታካይነትም ለምጣኔ ሃብትና ሰብዓዊ እርዳታ እንደሚውልም አንስተዋል።
ፕሬዚደንት ባይደን ዩክሬይንን ከሩስያ ወረራ መከላከል ርካሽ እንዳልሆነ ጠቁመው "እኛ ሩስያን አናጠቃም። እኛ ዩክሬይንን እየረዳን ያለው ራሷን ከሩስያ ጥቃት እንድትከላከል ነው" ብለዋል።

U.S. President Joe Biden gives remarks on providing additional support to Ukraine’s war efforts against Russia from the Roosevelt Room of the White House. Source: Getty