ሬሴፕ ጣይብ ኢርዶጋን ለተጨማሪ አምስት ዓመታት የተርኪዬ ፕሬዚደንት ሆነው ስልጣን ላይ የሚያቆያቸውን ዳግም ምርጫ በ 52.1 ፐርሰንት አሸነፉ።
አቶ ኤርዶጋን ከ2014 ጀምሮ ፕሬዚደንት፣ ቀደም ሲልም ለ11 ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን ቆይተዋል። ተቀናቃኛቸው የተቃዋሚ ቡድን መሪ ከማል ኪሊችዳህሮህሉ 47.9 ፐርሰንት ድምፅ በማግኘት ድል ተነስተዋል።
የተቃዋሚ ቡድን መሪው ውጤቱን አልቀበለም ባይሉም ምርጫ ፍትሕዊ አልነበረም ብለው ሲያማርሩ፤ የፕሬዚደንት ኢርዶጋን ደጋፊዎች በጎዳናዎች ላይ በመደነስ ደስታቸውን ገልጠዋል።
የእርዶጋንን ዳግም መመረጥ አስመልክቶ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን፣ የሩስያ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲንና የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚን ጨምሮ በርካታ የዓለም መሪዎች የመልካም ሥራ ዘመን ምኞት መግለጫዎቻቸውን ልከዋል።
ርዕደ መሬት
ሜልበርን ከ120 ዓመታት በኋላ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ገጥማት።
ከ 22,000 በላይ ሰዎች ጂኦሳይንስ አውስትራሊያ ዘንድ ደውለው የመሬት መንቀጥቀጥ እንደተሰማቸው ገልጠዋል።
ትናንት እሑድ ሜይ 28 በሜልበርን ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 11:41 pm የተከሰተው ርዕደ መሬት ከሜልበርን አልፎ እስከ ሰሜናዊ ቤንዲጎ እና ደቡብ ሆባርት ድረስ ዘልቋል።
የርዕደ መሬቱ መጠን 3.8 ማግኒቲዩድ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፤ እስካሁን በሳቢያው የደረሰ አደጋ አልተመዘገበም።