የትናንቱን ጥቃት አክሎ አል ሻባብ በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ ለሁለተኛ ጊዜ በኦክቶበር ወር ውስጥ ጥቃት አድርሷል።
አል ሻባብ ባደረሰው ጥቃት አንድ ወታደርን ጨምሮ የስምንት ሰላማዊ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱንና አምስት ሰዎች ለመቁሰል አደጋ መዳረጋቸውን የፖሊስ ቃል አቀባይ ገሳዲቅ አሊ ገልጠዋል።
ቃል አቀባዩ አያይዘውም፤ 60 ሰዎችን ታግተው ከነበሩበት ሥፍራ መታደግ መቻሉንና 6 የአል ሻባብ ሚሊሺያዎችን መግደሉን አስታውቀዋል።
ጥቃቱ የደረሰው ሞቃዲሾ ቦንዲሂር ወረዳ በሚገኘውና በፖለቲከኞችና በበርካታ ተጠቃሚዎች በሚዘወተረው ቪላ ሮዛ ሆቴል ነው።
ጥቃቱን ተከትሎ የሶማሊያ ፕሬዚደንት ሐሰን ሼክ መሐመድ ከመከላከያ ሚኒስትራቸው ጋር ኪስማዩ ያለው ጦራቸው ዘንድ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ቀጣናውን ከአሸባሪዎች ለማፅዳት ለሙሉ ዘመቻ ዝግጁ እንዲሆኑ መናገራቸው ተገልጧል።
አል ሻባብ ባለፈው ወር በሁለት ፈንጂ የተጠመዱ ተሽከርካሪዎች ሞቃዲሾ ውስጥ በሰነዘረው ጥቃት 120 ያህል ሰዎች ለሞት ሲዳረጉ፤ በተመሳሳይ ሁኔታ ከአምስት ዓመት በፊት ከ500 በላይ ሰዎችን ሕይወት አጥፍቷል።